የሀገር ውስጥ ዜና

የ2015 የ2ኛ ደረጃ ማጠቃለያ ፈተና ምዝገባ ከመጋቢት 20 እስከ ሚያዚያ 15 ቀን ይካሄዳል

By Alemayehu Geremew

March 27, 2023

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የ2015 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ማጠቃለያ ፈተና ምዝገባ ከመጋቢት 20 እስከ ሚያዚያ 15 ቀን 2015 ዓ.ም መሆኑን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አስታወቀ።

ከዚህ በፊት ይታዩ የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ የተሻሉ አሰራሮችን በመከተል ምዝገባው እንደሚካሄድ ተገልጿል።

አገልግሎቱ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ባለፉት ጊዜያት በፈተና አሰጣጡ ሂደት የአፈፃፀም ችግር በምዝገባ ሥርዓቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩን አስታውቋል።

ችግሮቹ በፈፃሚዎች ፣ በተመዝጋቢዎች ፣ በመዝጋቢዎች እና በትምህርት ቤቶች በጉልህ መታየታቸውም ነው የተመለከተው።

በወጣው የምዝገባ መርሐ-ግብር አለመመዝገብ ፣ የመመዝገቢያ ግብዓቶችን አሟልቶ አለመገኘት እና የምዝገባ ጊዜ ካለፈ በኋላ መምጣት በተመዝጋቢዎች ዘንድ የታየ ጉድለት ነበር ተብሏል።

በመዝጋቢዎች ደግሞ ለተመዝጋቢዎች ተገቢውን መረጃ አለመስጠት በትምህር ቤቱ ርዕሰ መምህር የተሰጣቸውን መመሪያ ባለመከትል ምዝገባ ማካሄድ እንዲሁም የተፈታኙን የግል ሁኔታ በተገቢው መንገድ አለመሙላት የታዩ ጉድለቶች መሆናቸውም ነው የተነገረው።

ትምህርት ቤቶችን በተመለከተ ከተነሱት ችግሮች መካከል ለምዝገባ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ግብዓቶች አለማማሟላት በዋናነት ተነስቷል።

ምዝገባው በበይነ መረብ የሚካሄድ በመሆኑ ትምህርት ቤቶች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸውም ተብሏል።

በዚህ መሰረት መደበኛ እና የማታ ተማሪዎች በሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች በመገኘት ምዝገባ ሚካሄድ የሚችሉ ሲሆን ለድጋሚ እና ለርቀት ትምህርት ተከታታዮች በተመረጡ የወረዳ ትምህርት ፅኅፈት ቤቶች በበይነ መረብ በቀጥታ ምዝገባ ያካሂዳሉ።

ከላይ በተመለከተው ቀን ያልተመዘገበ ማንኛውም ተፈታኝ ለፈተና እንደማይቀመጥም ነው አገልግሎቱ ያስታወቀው።

ከምዝገባ በኋላ የሚቀርቡ የሥም፣ የፆታ፣ የዕይታ፣ የፎቶ እና የትምህርት መሥክ ማስተካከያ ጥያቄዎች ተቀባይነት እንደማይኖራቸውም የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አስታውቋል።

በምንይችል አዘዘው