የሀገር ውስጥ ዜና

አስቸኳይ የፓስፖርት አገልግሎት ለጊዜው መቋረጡ ተገለጸ

By Alemayehu Geremew

March 28, 2023

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና መሥሪያ ቤት እንዲሁም በ11ዱ የክልል ቅርንጫፍ ፅኅፈት ቤቶች ሲሰጥ የነበረው “አስቸኳይ” የፓስፖርት አገልግሎት ለጊዜው መቋረጡ ተገለጸ፡፡

አገልግሎቱ የተቋረጠው ከአቅም በላይ የባለ ጉዳይ ፍሰት ከመፈጠሩ ጋር ተያይዞ መጠነ ሰፊ የሠነድ ማጭበርበሮች በመስተዋላቸው መሆኑን ነው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ያስታወቀው፡፡

በተጨማሪም ተገልጋዮች ሊገለገሉ ሌሊት በሚመጡበት ወቅት በተለያዩ ኅገ-ወጥ ግለሰቦች የሚደርስባቸው እንግልትና ጉዳት በአገልግሎት አሰጣጥ እና በተገልጋዩ ላይ ተግዳሮት በመፍጠሩ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ስለሆነም የማስተናገድ አቅምና ሌሎች ክፍተቶች እስከሚስተካከሉ ድረስ ይሰጥ የነበረው የ“አስቸኳይ”ፓስፖርት አገልግሎት ለጊዜው መቋረጡ ተገልጿል፡፡

ቀድሞ ይሰራበት በነበረው አሰራር መሰረት አስቸኳይ ጉዞ ያላቸው አገልግሎት ጠያቂዎች ማስረጃዎቻቸውን አቅርበው በዋና መስሪያ ቤቱ ብቻ ከመጋቢት 20 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የሚስተናገዱ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ተገልጋዮች ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ከኅገ ወጥ ደላሎች እንዲጠነቀቁም አገልግሎቱ አሳስቧል፡፡

የመደበኛ ፓስፖርት ተገልጋዮች ቀድሞ በነበረው ሒደት መስተናገድ እንደሚቀጥሉም የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡