አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል መንግስት ለጤና መድህን ፕሮግራም ማስፈጸሚ 13 ሚሊየን ብር አጽድቋል።
የሶማሌ ክልል የጤና መድህን ዋስትና ፕሮግራም ኮሚቴ ስብሰባ በዛሬው ዕለት በሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ ሰብሳቢነት በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ተካሂዷል።
በስብሰባው ላይ በክልሉ ለጤና መድህን ዋስትና ፕሮግራም ማስፈጸሚያ 13 ሚሊየን ብር መጽደቁን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በዚህም በክልሉ የጤና መድህን ዋስትና ፕሮግራም ተጠቃሚ ከተሞችና ወረዳዎችን ከአራት ወደ 10 ለማሳደግ እቅድ መያዙም ተገልጿል፡፡
ፕሮግራሙ በክልሉ ወረዳዎችና ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች በዓመት 325 ብር እና 500 ብር በመክፈል በተለይም የኑሮ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በተመጣጣኝ ዋጋ የተለያዩ የጤና አገልግሎቶችን ፍትሃዊ በሆነ ሁኔታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ተብሏል።
በሶማሌ ክልል የጤና መድህን ዋስትና ፕሮግራም በ2012 ዓመት በአውበሬ ወረዳ የተጀመረ ሲሆን÷ በአሁኑ ጊዜ ፕሮግራሙን በአራርሶ ፣ ኤረርና ጎዴ ከተማ አስተዳደር ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በዚህም 24 ሺህ 953 ቤተሰቦችና 164 ሺህ 690 አባላት በፕሮግራሙ ተጠቃሚ ለማድረግ መቻሉን የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ዘገባ ያመላክታል።