አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የቱሪዝሙን እንቅስቃሴ በማሳደግ የሚገኘውን ገቢም ለመጨመር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ቱሪዝም ኮሚሽን ገለጸ፡፡
የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ደራራ ከተማ (ረ/ፕሮፌሰር)÷ የመስኅብ ሥፍራዎችን በማልማት፣ ለጎብኚ ምቹ በማድረግ እና የክልሉን የመስኅብ ሃብት በማስተዋወቅ ረገድ በንቃት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
የማስተዋወቅ ሥራው ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ በርዋንዳ፣ ዛንዚባር፣ ጀርመን እና ፊንላንድ ጭምር መከናወኑን ገልጸዋል፡፡
የጎብኚ መዳረሻዎችን በማልማት ረገድም በክልሉ በዘርፉ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ልማት መኖሩን ተናግረዋል፡፡
በቱሪዝሙ ዘርፍ ኢንቨስት ለማድረግ ወደ ክልሉ ለሚመጡ አልሚዎች ሁኔታዎች እንደሚመቻቹም አረጋግጠዋል፡፡
ላለፉት ዓመታት በተለያየ ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረው የቱሪዝሙ እቅስቃሴ አሁን ላይ እየተነቃቃ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ ዘርፉን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት ወንጪ፣ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት እና የሶፍ ዑመር ዋሻ ላይ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ይጠቀሳሉ ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም የባቱ ከተማን በአርአያነት አንስተው÷ ከሌሎች መሠረተ ልማቶች ጋር ተጣምሮ አካባቢውን ለጎብኚ ምቹ ማድረግ በመቻሉ ውጤት መገኘቱን አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል አዳዲስ የቱሪዝም ምርት ወደ ገበያ እንዲቀላቀል እና ሕብረተሰቡ እንዲለማመደው እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው÷ ለምሳሌ በባቱ ከተማ እየተሠራበት ያለውን የዋይን ቱሪዝም ጠቅሰዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!