የሀገር ውስጥ ዜና

በአቶ አክሊሉ ታደሰ የተመራ ልዑክ በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የሥራ ጉብኝት እያደረገ ነው

By Shambel Mihret

April 03, 2023

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ የተመራ ልዑክ በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እያደረገ ነው፡፡

ይፋዊ የሥራ ጉብኝቱ ነፃ ንግድ ቀጠናን ከማልማት፣ ከማስተዳደር እና ከተያያዥ ጉዳዮች ጋር ውጤታማ ስራ ለመስራት ያለመ ነው ተብሏል፡፡

ልዑኩ በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ዲፒ ወርልድ ተቋም ዋና መስሪያ ቤት ተገኝቶ ከተቋሙ የመካከለኛ ምስራቅ እና አፍሪካ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሱሀኢል አልባና ጋር ተወያይቷል።

በውይይቱም የነፃ ንግድ ቀጠና ልማት፣ አስተዳደርና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ገንቢ ሀሳቦች ተነስተው መግባባት ላይ መደረሱን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠናን ውጤታማ ለማድረግ እንዲሁም ሌሎች ተጨማሪ ነፃ ንግድ ቀጠናዎችን ለማቋቋም ዓለም አቀፍ ልምድ እና አሰራሮችን ለመቅሰም በተለያዩ ሀገራት ይፋዊ ጉብኝት እና ግንኙነቶችን እየፈጠረ ይገኛል ተብሏል።