አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ ለድርቅ ተጋላጭ አካባቢዎች ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ በ30 ቢሊየን ብር የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ እንዳሉት÷ የክልሉ መንግስት የተከሰተውን የድርቅ አደጋ ለመቀነስ የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ አስቀምጦ እየተገበረ ይገኛል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በተከታታይ ዝናብ ባለመዝነቡ ሕዝቡ የድርቅ ተጋላጭ ሆኗል ብለዋል።
በዚሁ መሰረት በዋናነት ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያን መነሻ በማድረግ 10 የክልሉ ዞኖች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ለድርቅ ተጋላጭ መሆናቸውን አንስተዋል።
የክልሉ መንግስት እነዚህ ዜጎች በተለያዩ መልኩ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።
ለእነዚህ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፉን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር በክልሉ የድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ችግሩን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ መሆኑን አስታውሰዋል።
ፕሮጀክቶቹ ውኃ ማልማትን ማዕከል አድርገው አጠቃላይ የድርቅ ተጋላጭ ሕዝቦችን ኑሮ ማሻሻል ዓላማ ያደረጉ ናቸው ብለዋል።
አጠቃላይ የፕሮጀክቶቹ ወጪ 30 ቢሊየን ብር መሆኑን የገለጹት አቶ ሀይሉ ስራዎቹ በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
የሰብዓዊ ድጋፉን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የክልሉ መንግስት ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር የተለያዩ አካላት በስፋት እየተሳተፉበት መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዚህም ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በሰው ህይወት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ከማድረግ በተጓዳኝ እንስሳቱንም የመታደግ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ለድርቅ ከተጋለጡ የክልሉ ዞኖች አንዱ የሆነው የቦረና ዞን ዝናብ እየጣለ መሆኑ ትልቅ እገዛ መሆኑን ጠቅሰው በተገኘው እድል ውሃን የመያዝ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።