አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የቀድሞ ምክትል ኮሚሽነር ቱት ኮር በክልሉ ተፈጽሟል ከተባለ የንጹሃን ዜጎች ግድያ ጋር ተያይዞ ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቀረቡ።
በሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ/ም የሸኔ ሽብር ቡድን እና የጋምቤላ ነጻ አውጪ ፓርቲ በጋራ በመሆን በጋምቤላ ከተማ በፖሊስ ኮሚሽን ተቋም አካባቢ ባደረሱት ድንገተኛ ጥቃት መነሻ ለሽብር ቡድኑ መረጃ ሰጥተዋል በማለት ንፁሀን ዜጎች እንዲገደሉ የፖሊስ አባላትን ሰብስበው ትዛዝ ሰጥተዋል ተብለው መጠርጠራቸውን መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል።
በወቅቱ የፀጥታ አካላት በንፁሀን ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ እንደ አመራር ማስቆም ሲገባቸው ሳይስቆሙ በዝምታ አልፈዋል ሲል መርማሪ ፖሊስ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ገልጿል።
የምክትል ኮሚሽነሩን ቃል መቀበሉን የገለጸው መርማሪ ፖሊስ በተጠረጠሩበት ወንጀል ማስረጃ እየሰበሰበ መሆኑን ተናግሯል።
ተጨማሪ ማስረጃ ለማሰባሰብ፣ የኤሌክትሮኒክ ምርመራ ውጤት ለማቅረብ እና የምስክር ቃል ለመቀበል የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱን ጠይቋል።
ተጠርጣሪው በበኩላቸው÷ በወቅቱ ወንጀሉ ሲፈጸም የክልሉን ፕሬዚዳንት ጨምሮ የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊው ነበሩ ፤ ንፁሃን ላይ ጥቃት እንዲደርስ ምንም ዓይነት ትዕዛዝ አልሰጠሁም ሲሉ ተከራክረዋል።
የኛ ወታደሮች ወደ ሱዳን ድንበር እየገቡ ስለሆነ ይጠርነፉ (ይታሰሩ) የሚል ሐሳብ ብቻ ነው የገለፅኩት እንጂ ምንም ትዕዛዝ አልሰጠሁም ሲሉም አስረድተዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ በወቅቱ እሳቸውን ጨምሮ በሌሎች አመራሮች ላይ ግምገማ መካሄዱን አስገንዝበዋል፡፡
ለ25 ዓመታት ሀገሬን በታማኝነት አገልግያለሁ ያሉት ተጠርጣሪው÷ ወደ ስፖርት ኮሚሽን መዘዋወራቸውን ጠቅሰው ለችሎቱ አብራርተዋል፡፡
ወደ ኡጋንዳ ለሥራ ተልኬ ሄጄ ነበር፤ ምንም ወንጀል ስላልሰራሁ ነው ወደ ሀገሬ ተመልሼ የመጣሁት፤ መጥፋት ብፈልግ ኖሮ ተመልሼ አልመጣም ነበር ሲሉም ነው ያስረዱት፡፡
ከዚህ በፊት በአጋጠማቸው የጤና እክል ምክንያት ቀዶ ጥገና እንደተደረገላቸው የሚገልጽ የሕክምና ማስረጃ ለዳኛው አሳይተዋል።
ፍርድ ቤቱ ያሉበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ አስገብቶ የዋስ መብቴን ያክብርልኝ ሲሉም ጠይቀዋል።
በወቅቱ የነበረውን አጠቃላይ ሁኔታ የሚገልጽ በተንቀሳቃሽ ምስል የተደገፈ ማስረጃን ፍርድ ቤቱ እንዲመለከትላቸውም ጠይቀዋል።
የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡን የተመለከቱት ዳኛ ÷ ተጠርጣሪው በዋስ ቢወጡ ምን ሊፈጥሩ ይችላሉ? ሲሉ ለፖሊስ የማረጋገጫ ጥያቄ አቅርበዋል።
ፖሊስ በበኩሉ÷ በዋስ ቢወጡ ከነበራቸው ተቀባይነት አንጻር ምስክር ሊያሸሹብን ይችላሉ ሲል መልስ ሰጥቷል።
አጠቃላይ ክርክሩን የተከታተለው የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የተጠርጣሪውን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው ውድቅ በማድረግ ተጨማሪ ማስረጃ ማሰባሰብ አስፈላጊነትን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለፖሊስ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።
በታሪክ አዱኛ