የሀገር ውስጥ ዜና

በትግራይ ክልል ያሉ የመስኅብ ሥፍራዎችን ሁኔታ ለማጥናት ቅድመ ዝግጅት ተጀመረ

By ዮሐንስ ደርበው

April 05, 2023

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በነበረው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ለተወሰኑ ዓመታት ክትትል ያልተደረገባቸው የመስኅብ ሥፍራዎች ያሉበትን ሁኔታ ለማጥናት የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጀመሩን ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ሚኒስቴሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጸው÷ በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ሲስተካከል ቅርሶችና ፓርኮች እንዲሁም ሌሎች መዳረሻዎች በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ በዝርዝር ለማጥናት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅትም ጥናቶችን ለማካሄድ የሚያስችሉ መሣሪያዎች እየተዘጋጁ መሆኑን ነው የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ የተናገሩት፡፡

የጥናቱን ውጤት መሰረት በማድረግም ሚኒስቴሩ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ እና የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣኖችን በመያዝ ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

እንዲሁም ከግጭቱ በኋላ በአማራ እና አፋር ክልሎች ከቱሪዝሙ ዘርፍ ጋር በተያያዙ ያሉ ጉዳዮች እንዲጠኑ በተጀመረው እንቅስቃሴ መሠረት÷ የጥናቱን ውጤት መሠረት በማድረግ ድጋፍ ማድግ ተጀምሯል ብለዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በተጠሪ ተቋማቱ አማካኝት ለቱሪዝሙ ዕድገት በትኩረት እየሠራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በተለይም ከመሬት ይዞታ ጋር የተያያዙ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ፣ ፓርኮቹን በዘላቂነት ለመጠበቅ እና ምን ዓይነት ስትራቴጂ መከተል ይገባል የሚለውን ታሳቢ በማድረግ የተወሰኑ ፓርኮች የአስተዳደር ፕላን እዲኖራቸው መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

ይህ አሠራርም ወደ ሁሉም ፓርኮች እንደሚሰፋ አረጋግጠዋል፡፡

ቅርሶች ሙሉ በሙሉ ከመጎዳታቸው በፊት በወቅቱ የጥገናና ጥበቃ ሥራዎች እንዲጠናክሩ፣ ከመጠበቅ ጎን ለጎንም ቅርሶቹ ለማሕበረሰቡ የሥራ ዕድል ፈጥረው ተጠቃሚነት እንዲያመጡ፣ ቢያንስ የራሳቸውን የጥገና ወጪ እንዲያመነጩ የጥበቃ ስትራቴጂ ተቀርጾ መተግበር ጀምሯል ብለዋል፡፡

በላሊበላ አካባቢ ያሉ 22 የተመረጡ አስቸኳይ ጥገና ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን፣ በጢያ ትክል ድንጋይ አካባቢ የጥበቃ ሥራዎች መከናወናቸውን እና በጅማ አካባቢም እየተሠሩ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል የአስተዳደር ፕላን እና የጥበቃና እንክብካቤ ዕቅድ መዘጋጀቱን ጠቁመው÷ በዚህም በነበረው አሠራር ላይ የተለያዩ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ቀደም ሲል ቅርሶች ይጠበቁ የነበሩት በቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ብቻ እንደነበር አስታውሰው÷ አሁን ግን ክልሎች መጠገን እና መንከባከብ ከፈለጉ መብት እንዲሰጣቸው የአዋጅና መመሪያ ማሻሻያ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ቅርሶች እና የተፈጥሮ ሃብቶች ባሉበት አካባቢ ለማሕበረሰቡ የሥራ ዕድል የሚፈጥር፣ የቅርሶቹን ፣ የፓርኮቹን ማንነት እና ያላቸውን አጠቃላይ ሃብት ዕሴት ታሪክ በማይነካ መንገድ ለአገልግሎት የሚውሉበት አሠራርም በስትራቴጂው መቀረጹን ነው ያመላከቱት፡፡

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!