የሀገር ውስጥ ዜና

አካል ጉዳተኞችን ያገናዘበው የሕንጻ አዋጁ አተገባበር ክትትል ያስፈልገዋል ተባለ

By Alemayehu Geremew

April 05, 2023

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ያወጣውን የሕንጻ አዋጅ አተገባበር እንዲከታተል ተገልጋዮች ጠየቁ፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የአካል ጉዳተኛ ዜጎች ፍላጎቶች ከሕንጻ ግንባታና ሌሎች ከሚያነሷቸው አንገብጋቢ ጥያቄዎች አንጻር ምን ያህል ተሟልቷል የሚለውን ጥያቄ በመያዝ አካል ጉዳተኞችን አናግሯል፡፡

አካል ጉዳት የደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችም አብዛኛውን ጊዜ አገልግሎት ለማግኘት በሚሄዱባቸው መሥሪያ ቤቶች እነርሱን ያማከለ አገልግሎት ለማግኘት እንደሚቸገሩ አንስተዋል፡፡

የበርካታ መሥሪያ ቤት ህንጻዎችም አካል ጉዳተኛ ያልሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ብቻ ታሳቢ ያደረጉ ይመሥላሉ ብለዋል፡፡

አካል ጉዳተኞቹ አገልግሎት ለማግኘት በሚሄዱባቸው መሥሪያ ቤቶች አብዛኛውን ጊዜ አሳንሰሮቹ ከ3ኛ ፎቅ በላይ ብቻ እንዲሠሩ ይደረጋል ነው ያሉት።

ይህ መሆኑ ደግሞ አገልግሎት ፈልገው ለሚሄዱ አካል ጉዳተኞች እና ዐቅመ-ደካሞች ደረጃዎችን የመውጣት ፈተና ውስጥ እንደሚከታቸው ነው ያስረዱት።

በመሆኑም መንግስት በኅንጻዎቻቸው ውስጥ አሳንሰሮች እያላቸው ሆነ ብለው አገልግሎት እንዳይሠጡ የሚያደርጉ የመንግስት እና የግል አገልግሎት ሠጪ ተቋማት ላይ ክትትል አድርጎ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡

በተጨማሪም ኅንጻዎች ሲገነቡ የወንድ እና የሴት ተብሎ የመፀዳጃ ቦታዎች ተለይተው እንደሚመላከቱ ሁሉ አካል ጉዳተኞችንም ታሳቢ የሚያደርጉ ልዩ መጸዳጃ ቤቶች እንዲኖራቸው ቢደረግ መልካም መሆኑን ያነሳሉ፡፡

በሌላ በኩል መንግስት ለከተማዋ ነዋሪዎች የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ሲገነባ በዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለአካል ጉዳተኞች ቅድሚያ እንደሚሰጥ የተነገረ ቢሆንም፥ በ2005 ዓ.ም ቁጠባ ጀምረው እስካሁን ዕጣ እንዳልወጣላቸው የገለጹ አካል ጉዳተኞችም ነበሩ፡፡

ከአንድ ወር በፊት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በጉዳዩ ላይ በሰራው ዜና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን በመጀመሪያው ግማሽ በጀት ዓመት በ217 ሕግ ተላልፈው የተገኙ አልሚዎች ላይ ከ350 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ጀምሮ የማስጠንቀቂያ እና የሥራ ፈቃድ መሠረዝ እርምጃዎች መውሰዱን መዘገቡ ይታወሳል፡፡

በዓለማየሁ ገረመው