የሀገር ውስጥ ዜና

በአዲስ አበባ የጎዳና ላይ ኢፍጣር ለ3ኛ ጊዜ እንደሚካሄድ ተገለጸ

By Alemayehu Geremew

April 05, 2023

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጎዳና ላይ ኢፍጣር የፊታችን ቅዳሜ መጋቢት 30 ቀን ለ3ኛ ጊዜ እንደሚካሄድ ተገለጸ።

የጎዳና ላይ ኢፍጣሩ “ኢፍጣራችን ለወገናችን” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እንደሚካሄድም ተጠቁሟል፡፡

ረመዳን የአብሮነት ፣ የመረዳዳት እንዲሁም የዕዝነት ወር እንደመሆኑ በዕለቱ ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ ይሰባሰባል ተብሏል።

በአፍጥር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ህዝበ ሙስሊሙ ለአፍጥር በቤት ያዘጋጀውን ይዞ በመገኘት የወንድማማችነት ግንኙነቱን እንዲያጠናክር ጥሪ ቀርቧል።

ሥነ-ሥርዓቱን የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ከነጃሺ በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን ይመራዋል።

መርሐ-ግብሩ የተሳካ እንዲሆን በዕለቱ ከ4 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡

በፈቲያ አብደላ