አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ወገኖች ከሐምሌ ወር ጀምሮ በተለያዩ አካላት ድጋፍ እየቀረበ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
በዚህም በፌደራል መንግስትና በወርልድ ቪዥን አማካኝነት ከ498 ሺህ 816 ኩንታል በላይ እህል፣ ከ10 ሺህ 974 ኩንታል በላይ ጥራጥሬ እና ከ3 ሺህ 271 ኩንታል በላይ ዘይት ለ1 ሚሊየን 658 ሺህ 34 ዜጎች መሰራጨቱ ተገልጿል፡፡
በአደጋ ጊዜ ምላሽ ሰጪ ሴፍቲኔት በኩልም ለ294 ሺህ 646 ሰዎች ከ207 ሚሊየን 244 ሺህ ብር በላይ ቀርቦ በሁለት ወረዳዎች መሰራጨቱን እና በ13 ወረዳዎች እየተሰራጨ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
በፌደራል መንግስት በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም አማካኝነት ከሐምሌ ወር ጀምሮ ለ113 ሺህ 641 ቀጥታ ተጠቃሚዎች እንዲሁም ከጥር ወር ጀምሮ ለ803 ሺህ 721 የማህበረሰብ ስራ ተሳታፊዎች ከ545 ሚሊየን 24 ሺህ ብር በላይ ተሰራጭቷል ተብሏል፡፡
በክልሉ መንግስት 26 ሺህ 409 ኩንታል በቆሎ ተገዝቶ መቅረቡን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ስሩር ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም የህብረተሰቡን የእርስ በርስ የመደጋገፍ ባህል መሰረት በማድረግ የእርስ በርስ ለመደጋገፍና ለችግር ተጋላጭ ወገኖችን ለመታደግ በተደረገው ርብርብ ከ30 ሺህ 344 ኩንታል በላይ እህል ድጋፍ መደረጉን ነው የገለጹት፡፡
በ48 ወረዳዎች በዓለም ምግብ ፕሮግራም ለ330 ሺህ 176 ሕጻናትና እናቶች 35 ሺህ 684 ኩንታል አልሚ ምግብ እየቀረበ መሆኑን ነው አቶ ኡስማን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት፡፡
በዮሐንስ ደርበው
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!