አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ186 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠቱን የኦሮሚያ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቢሮው ኃላፊ አቶ አህመድ ኢድሪስ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ÷ ከ 186 ቢሊየን ብር ካፒታል በላይ ላስመዘገቡ 3 ሺህ 600 በላይ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል ብለዋል፡፡
ፍቃድ ከተሰጣቸው መካከልም 92 የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ጥያቄ ያቀረቡ ፣ 1 ሺህ 502 ወደ ኢንቨስትመንት የተሸጋገሩ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ፣ 47 ዩኒየኖች እንዲሁም 1 ሺህ 680 የሀገር ውስጥና የዳስያስፖራ ባለሃብቶች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል፡፡
ባለሃብቶቹ በሙሉ አቅማቸው ወደስራ ሲገቡ ከ679 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥሩም አቶ አህመድ መናገራቸውን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።