ጤና

የሕጻናት ምግብ ፍላጎት መቀነስን እንዴት ማስተካከል ይቻላል?

By Amele Demsew

April 06, 2023

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕጻናት ላይ የሚስተዋለውን የምግብ መቀነስ በወላጆች ንቁ ክትትል በቀላሉ ማስተካከል እንደሚቻል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ተፈጥሯዊ የምግብ ፍላጎት መቀነስ ፣ የተለያዩ ህመሞች፣ የንጥረ ነገሮች እጥረት፣ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብና የአመጋገብ ልምምድ ለሕጻናት የምግብ መቀነስ ምክንያት እንደሆኑ የሕጻናት ስፔሻሊስት ዶ/ር ፀጋዬ ተኒ ገልጸዋል፡፡

የተለያዩ ህመሞች ሲባል÷ ጥርስ ማብቀል፣ የቶንሲል፣ የአንጀት፣ የሽንት ቧንቧ፣ የጆሮ ኢንፌክሽን፣ የአንጀት ጥገኛ ትላትሎች፣ የልብ፣ የነርቭ፣ የኩላሊት፣ የጉበት ህመም፣ ደም ማነስ እና የጨጓራ ህመምን ያጠቃልላል ብለዋል፡፡

በአብዛኛው ምክንያቱ በምግብ እጥረት እና የላም ወተትን ያለጊዜው በመጀመር (አብዝቶ በመስጠት) የሚከሰተው በአይረን እጥረት የሚመጣ የደም ማነስ ለሕጻናት የምግብ ፍላጎት መቀነስ ሌላ መንስኤ ነው ይላሉ፡፡

የቫይታሚኖች፣ ማግኒዥየም፣ ካልሺየም፣ ዚንክ እና ሌሎች ንጥረ ነገሮች እጥረት ለምግብ ፍላጎት መቀነስ አጋላጭ መሆናቸውን ጠቁመው÷ እጥረቶቹን ለማስተካከልም የደም ምርመራ እንደሚስፈልግ ይመክራሉ፡፡

ጭማቂ፣ ወተት፣ አጥሚት፣ ጣፋጭ ነገሮች፣ የታሸገ እና ፈሳሽ ምግብ ከአንድ ዓመት በላይ ለሆናቸው ሕጻናት አብዝቶ መስጠት የሕጻናትን የምግብ ፍላጎት እንደሚቀንስ ባለሙያው አብራርተዋል፡፡

ከ 2 እስከ 6 ዓመት የሆናቸው ሕጻናት በቀን ከ 120 እስከ 180 ሲ ሲ (ከ2 እስከ 3 የቡና ስኒ) በላይ ጭማቂ መውሰድ እንደሌለባቸው መክረዋል፡፡

ሕጻናት በተደጋጋሚ ጣፋጭ ነገሮችን ከወሰዱ ምግብ የመመገብ ፍላጎታቸው እንደሚቀንስ እና ለአላስፈላጊ ውፍረት እንደሚያጋልጡ ስፔሻሊስቱ አንስተዋል፡፡

የሕጻናት የአዕምሮ እና የአካል ዕድገት እንዲፋጠን፣ ሰውነታቸው ጠንካራ እንዲሆን እንዲሁም የተመገቡት ምግብ በአግባቡ እንዲፈጭ በቀን ቢያንስ ከ30 እስከ 60 ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ይመከራል፡፡

በአንድ ዓመታቸው እስከ 7 ኪሎ ግራም በዓመት ሊጨምሩ እንደሚችሉ ገልጸው÷ ሁለተኛ ዓመታቸው ላይ ግን በተፈጥሮ የሚጨምሩት 2 ኪሎ ግራም በመሆኑ በዚህ ምክንያት የምግብ ፍላጎት መቀነሱ ተፈጥሯዊ ነው ይላሉ።

የምግብ ፍላጎታቸውን ለመጨመር የሚወሰዱ መፍትሔዎች ለሁሉም ሕጻናት እኩል ላይሠሩ ስለሚችሉ የምግብ ፍላጎት የቀነሰበትን ምክንያት መለየቱ ዐቢይ ጉዳይ መሆኑን ያስገነዝባሉ፡፡

በአጠቃላይ ግን ምግብ ለማስለመድ ሲያስቡ ከ15 እስከ 20 ጊዜ በትዕግስት መሞከር በተለይም ከ 6 እስከ 12 ወር ላሉ ሕጻናት ሁሉንም የምግብ ዓይነት ጣዕም ቀስ በቀስ ማስለመድ አስፈላጊ መሆኑን ነው የመከሩት፡፡

እንዲሁም ምግቡን ፊትለፊታቸው በማስቀመጥ እንዲነኩት እና እንዲቀምሱት ይህንንም በየቀኑ ቢያንስ ከ15 እስከ 20 ጊዜ መሞከር እንደሚስፍልግም ነው ዶ/ር ፀጋዬ ያስረዱት፡፡

ሕጻናት አንድን ምግብ አንፈልግም ስላሉ ብቻ ተለዋጭ ምግብ ለማቅረብ መቸኮል ተገቢ አለመሆኑን ጠቅሰው÷ ያንኑ ምግብ ደጋግሞ በማቅረብ አልፈልግም ሲሉ በማንሳት ውጤት ማምጣት ይቻላል ነው ያሉት፡፡

ቋሚ የምግብ ሰዓትን አለማስለመድ፣ ጣፋጭ ነገርን አለማብዛት፣ ትኩረት የሚወስዱ ነገሮችን በማስወገድ (ቴሌቪዥን፣ ስልክ)፣ ለዓይን የሚስቡ ምግቦችን በማዘጋጀት የሕጻናትን የምግብ ፍላጎት ለማስተካከል እንደሚያግዙ ነው ባለሙያው ያስገነዘቡት፡፡

በአመለወርቅ ደምሰው