የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ስደተኞችን በማስጠለል እየፈጸመች ላለችው በጎ ተግባር ድጋፋን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ገለጸ

By Amele Demsew

April 06, 2023

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ወደ ግዛቷ ለሚመጡ ስደተኞች መጠለያ በመሆን እየፈጸመች ላለችው በጎ ተግባር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ገልጿል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የዓለም አቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት የምስራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ሞሐመድ አብዲከር፥ ኢትዮጵያ በሚሊየን የሚቆጠሩ የተለያዩ ሀገር ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ የምትታወቅ መሆኗን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የስደተኞች አያያዝ እያሳየች ያለችው መልካም ተግባር የሚያስመሰግናት መሆኑንም ተናግረዋል።

ሀገሪቱ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር እያደረገች ላለው የሰብአዊ እርዳታና የመጠለያ አቅርቦት ድርጅቱ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

ድርጅቱ ኢትዮጵያ ከፍልሰት ጋር በተያያዘ በድንበር አስተዳደር ላይ ለምታከናውናቸው ተግባራት የአቅም ግንባታ ስልጠና እና ሌሎች ድጋፎችን እያደረገ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በፍልሰት ዙሪያ ያላትን ትብብር አድንቀው፥ ድርጅቱ ኢትዮጵያ ያላትን የመሪነት ሚና ለመደገፍም ቁርጠኛ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ተጠልለው ለሚገኙና ሰብአዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ፍልሰተኞች ለጋሽ ድርጅቶች ትብብር እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።