አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፓኪስታን የኢትዮያ አምባሳደር ጀማል በከር ከሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሴክሬታሪ አሳድ መጅድ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ሀገራቱ ያላቸውን የሁለትዮሽና ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡
አምባሳደር ጀማል በከር÷ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ ህግ በሆነው ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ምክንታዊና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በመጠቀም መርሕ እንደምታምን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የቀጠናውን ሀገራት በሃይል ለማስተሳሰር ከፍተኛ ሚና ያለውን የታላቁ ሕድሴ ግድብ ዓለም አቀፋዊ የግንባታ መስፈርቶችን መሰረት በማድረግ እየገነባ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ከታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ጋር ያለውን ልዩነት ለመፍታትም ኢትዮጵያ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም መርሐን እንደምትከተል አስገንዝበዋል፡፡
በተጨማሪም አምባሳደ ጀማል በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በዚህም ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን የመልሶ ማቋቋም እና ግንባታ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አብራተዋል፡፡
ባሳለፍነው ወር በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጭ ለመመልከት የመጡት የፓኪስታን ባለሃብቶች ልዑክም የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ይበልጥ ያስተሳሰረ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ዶክተር አሳድ መጅድ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ መንግስት በፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ እያከናወነ ያለውን ስራ አድንቀዋል፡፡
ፓኪስታን በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም እና ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንደምታግዝም አረጋግጠዋል፡፡
በውይይቱ በሚቀጥለው ወር የኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ልዑክ በፓኪስታን በሚያደርገው ጉብኝት ዙሪያ ምክክር መደረጉም ተጠቁሟል፡፡
#Ethiopia ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!