አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 29 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚተዳደሩበት ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በተሰጠው ስልጣን መሰረት ክልሎች ከሚጠቀሙባቸው አዋጆች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ አዋጆችን እንዲያወጡና እንዲያፀድቁ ሲሰራ ቆይቷል፡፡
እስከ አሁንም አምስት ክልሎች ባለስልጣኑ ከሚጠቀምባቸው አዋጆች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ አዋጆችን አፅድቀው ወደ ስራ ገብተዋል።
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንደገለፁት አዋጁ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ያነሷቸው የነበሩ ቅሬታዎችን ሊፈታ የሚችልና ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በሀላፊነት እንዲከውኑ የሚያስችል ነው ብለዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለሀገረ መንግስት ግንባታ አጋር ናቸው ያሉት አቶ ፋሲካው ለድርጅቶቹ ምቹ ሁኔታን መፍጠርና ድጋፍ ማድረግም ከመንግስት ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊው አያሌው ቢሻው (ዶ/ር) በበኩላቸው ረቂቅ ህጉ አሳሪ የሆኑ አሰራሮችን በማስተካከል ድርጅቶቹ ለማህበረሰቡ በቂ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
በረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነትና አተገባበር ዙሪያ ባለድርሻ አካላት ከተወያዩ በኋላ እንዲፀድቅ ይደረጋልም ተብሏል።
በሙሉጌታ ደሴ