አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ሊታረስ ከሚችለው 74 ሚሊየን ሄክታር ውስጥ እየታረሰ ያለው 16 ሚሊየን ሔክታር መሬት ብቻ መሆኑ ተመለከተ፡፡
የአፈር አሲዳማነትን በማከም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ያተኮረ ውይይት በቦንጋ ከተማ እየተካሔደ ነው፡፡
በውይይቱ ላይ የቀረበ ጥናት እንዳመላከተው÷ እየታረሰ ካለው መሬት 7 ሚሊየን ሔክታሩ በአሲዳማ አፈርነት እንዲሁም 3 ሚሊየን ሔክታሩ በጠንካራ አሲዳማነት ተጠቅቷል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)÷ በክልሉ ካለው 3 ነጥብ 9 ሚሊየን ሔክታር 21 በመቶው አሲዳማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የግብርና ምርትን ለማሻሻል ጥረት ቢደረግም በዚህ ምክንያት ውጤት ሊመጣ አልቻለም ብለዋል፡፡
አሲዳማ አፈርነትን ለማከምም የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)÷ በሀገሪቱ ይህን ያህል መሬት በአፈር አሲዳማነት መጠቃቱ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በፍጥነት ወደ መፍትሄ መሻገር እንደሚያስፈልግ ገልጸው÷ ክልሎች በጉዳዩ ላይ በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡
አሲዳማ አፍርነትን ለማከም የሚያስፈልጉ ኖራ አምራች ማሽኖች በክልሎች እንዲኖሩም ይሠራል ነው ያሉት፡፡
በፍሬው ዓለማየሁ