አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢራን በሳዑዲ ዓረቢያ ኤምባሲዋን ዳግም ስራ ለማስጀመር የቴክኒክ ልዑክ ወደ ሪያድ በተያዘው ሳምንት ልትልክ መሆኑን አስታውቃለች፡፡
ኢራን እና ሳዑዲ ዓረቢያ ከሰባት ዓመታት ባላንጣነት በኋላ በቻይና አሸማጋይነት ወደ ቀደመ ግንኙነታቸው ለመመለስ መስማማታቸው ይታወሳል፡፡
ባሳለፍነው ሐሙስ ዕለትም የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቻይና ቤጂንግ ከሳባት ዓመታት በኋላ መደበኛ ውይይት ማድረጋቸው ተጠቁሟል፡፡
ይህን ተከትሎም ኢራን በሳዑዲ ዓረቢያ ኤምባሲዋን ዳግም ለመክፈት የቴክኒክ ልዑክ ወደ ሪያድ በተያዘው ሳምንት እንደምትልክ አስታውቃለች፡፡
ልዑካኑ በቆይታቸውም ኤምባሲውን ዳግም ስራ ማስጀመር የሚያስችሉ በርካታ ስራዎችን ያከናውናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ቲ አር ቲ ዘግቧል፡፡
ከዚህ ባለፈም የሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ቀደመ ሁኔታው መመለስ የሚያስችል ውይይት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚያደርጉ ተመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ የሳዑዲ ባለስልጣናት በኢራን የሀገሪቱን ኤምባሲ ዳግም መክፈት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በቴህራን ጉብኝት ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡