የሀገር ውስጥ ዜና

በጋምቤላ ክልል የልዩ ኃይል አደረጃጀታዊ መዋቅርን የማስፈጸም ተግባራዊ ስራ ተጀምሯል – የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን

By Amele Demsew

April 09, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል በመንግስት የተጠናው የልዩ ኃይል አደረጃጀታዊ መዋቅርን የማስፈጸም ተግባራዊ ስራ መጀመሩን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰናይ አኩዎር የልዩ ኃይል አደረጃጀቱን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት÷ በመንግስት የተጠናውን አዲሱን የልዩ ኃይል አደረጃጀት ተግባራዊ የማድረግ ስራ ተጀምሯል።

በአሁኑ ወቅት የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት በሚፈልጉት የጸጥታ መዋቅር ለመደራጀት ምዝገባ እያካሄዱ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ከክልልና ከፌዴራል የጸጥታ አካላት የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሞ የልዩ ኃይል አባላት ወደሚፈልጉት የፖሊስና የሀገር መከላከያ ሰራዊት መዋቅሮች የማደራጀት ስራ እየተሰራ ነው ማለታቸውን ኢዘኤ ዘግቧል።

በተመሳሳይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት የተጀመረው ሥራ የሀገርን ሉዓላዊነት እና የሕዝቦችን ሠላም የሚያረጋግጥ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ሁሉም ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ስታውቋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ልዩ ኃይል ከሀገር መከላከያ፣ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከተለያዩ ክልሎች ልዩ ኃይሎች ጋር በመሆን ለሀገር እና ለክልሉ ሠላም መረጋገጥ የከፈለው ዋጋ ሁሌም በጀግንነት የሚታወስ ነው ብሏል ኮሚሽኑ፡፡

የአደረጃጀት ትግበራውም ህገ-መንግስቱን መሠረት ያደረገ፣ በጥናት ላይ የተመሠረተ እና ከክልል መንግስታት ጋር በተደረገ ውይይት ላይ የተመሠረተ ስለመሆኑም ተጠቁሟል።

ውሳኔው ሠፊ ውይይት የተደረገበት እና የክልል የልዩ ኃይል አባላትም እንደየፍላጎታቸው መከላከያ ሰራዊት፣ በፌዴራል ፖሊስ እና በመደበኛ ፖሊስነት ተቀላቅለው ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉ የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የክልሉን ልዩ ኃይል መልሶ ለማደራጀት የተቀመጠውን አደረጃጀት ለማስፈጸም በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልም ወደ ተግባር የተገባው የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ሥራ በመገባደድ ላይ እንደሚገኝ የክልሉ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታውቋል፡፡

እንደሀገር የክልል ልዩ ኃይሎች አደረጃጀት መልሶ የማደራጀት ስራው በፌዴራልና በክልሎች ህገ መንግስት በተቀመጠውና ጥናቱን ተከትሎ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት መልሶ ማደራጀት የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸን ተጠቁሟል።

በዚህም ከክልሉ ጀምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ አመራሩ፣የጸጥታ መዋቅሩ፣ የልዩ ኃይል አመራሩና መላው አባላት ጋር ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ መደረሱንና ልዩ ኃይሎች የተቀመጣላቸው አማራጮች መነሻ በማድረግ ፍላጎታቸውን የመለየት ስራ ተጠናቅቋል ነው የተባለው፡፡

በቀጣይም በመረጡት ምርጫ መሰረት ተቋማቱ ያወጡት መስፈርቶችን ተከትሎ ቀጣይ ስራዎች እንደሚከናወኑ የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡