የሀገር ውስጥ ዜና

በይርጋለም የተቀናጀ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ ያሉ ኩባንያዎች ውጤታማ እየሆኑ ነው – ኮርፖሬሽኑ

By Amele Demsew

April 09, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ የገቡ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ለገበያ በማቅረብ ላይ ውጤታማ መሆናቸውን የሲዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ።

ኩባንያዎቹ የተቀነባበረ የወተትና የፍራፍሬ ጭማቂዎችን በማምረት ምርቶቹን ለሀገር ውስጥ ገበያና ወደ ተለያዩ የውጭ ሀገራት ገበያዎች በመላክ መጀመራቸው ተጠቁሟል።

የሲዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቢዝነስ ልማትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጴጥሮስ ጳውሎስ እንዳሉት÷ በፓርኩ ከ6 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች በተለያዩ መስኮች ለመሰማራት ፈቃድ ወስደዋል።

ፈቃድ ከወሰዱ ባለሃብቶች መካከል ስድስቱ የወተትና የፍራፍሬ ጭማቂዎችን በማምረት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለይም የአቮካዶ ዘይት፣ ቡና፣ ወተትና የፍራፍሬ ጭማቂ ማምረት ላይ መሆናቸውን ገልጸው ÷ ኩባንያዎቹ ምርቶቻቸውን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ኩባንያዎቹ ባለፉት ሁለት ዓመታት ወደውጭ ሀገራት ገበያ ከላኩት ምርት ከ6 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ የአሜርካን ዶላር ገቢ ማስገኘታቸውን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ÷ ከ6 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውን ተናግረዋል።

በፓርኩ ወደፊት 152 ኩባንያዎች ማስተናገድ የሚችሉ ሼዶች እንደሚኖሩት የተገለጸ ሲሆን÷ እስከ 400 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች ስራ ይፈጥራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

#Ethiopia ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!