የሀገር ውስጥ ዜና

የቅባት እህል አምራቾችን ከዘይት አምራቾች ጋር የሚያገናኝ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው

By Tamrat Bishaw

April 10, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቅባት እህል አምራቾችን ከዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር የሚያገናኝ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።

ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ግብርና ሚኒስቴር እና ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በጋራ ባዘጋጁት የውይይት መድረክ÷ የቅባት እህል አመራረት፣ ምርትና ምርታማነት ለመጨመር እና የግብአት አቀራረብ ችግሮች ዙሪያ ተወያይቶ ለመፍታት እንዲሁም ትስስርን ለመፍጠር ያለመ ነው ተብሏል።

የግብርና ዘርፉ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለግብርና ማቀነባበርም የጥሬ ዕቃ ምንጭ በመሆን 33 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ጠቅላላ ምርት እድገትን የሚሸፍን መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ከሚመረቱት የሰብል እህሎች ውስጥ 68 በመቶ የሚሆነው የጥራጥሬ እህሎች ናቸው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው የቅባት እህሎችን ለማምረትና ፕሮሰስ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ቢኖርም አልተሰራበትም ብለዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሀመድ እና የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተሻለ በልሁ ከአመራረት ጀምሮ ለኢንዱስትሪ ግብአትነት ድረስ ባለው ሂደት ውስጥ የጥራት መጓደል ችግሮች መኖራቸውን አንስተዋል።

በመሆኑም ከዘይት ፋብሪካ ባለቤቶች ጋር በመወያየት ችግሮችን መቅረፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የምርታማነት መጠንን መጨመርና ግብይቱ ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የገበያ ትስስር የሚፈጠርበት ሁኔታ ላይ መምከር እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።

በቀረበው የውይይት ሰነድ ላይ ኢትዮጵያ የቅባት እህሎችን በማምረት በአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃን እንደምትይዝ ተገልጿል።

ለዘይት ምርት የአኩሪ አተር፣ የሰሊጥ እና በተለይም አኩሪ አተርን ማስፋፋት ከምርቱ ባለፈ የአፈር ለምነትን ለመጨመር የተመረጠ ሆኖ በስፋት እየተሰራበት ነው ተብሏል።

በማርታ ጌታቸው