አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 4ሺህ 392 ካሬ ሜትር ይዞታን ያለአግባብ ለግለሰቦች እንዲሰጥ በማድረግ ከ132 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ ወንጀል የተጠረጠሩ 48 ተከሳሾች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ።
ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ነው።
የፍትኅ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ48 ተከሳሶች ላይ የተሳትፎ ደረጃቸውን ጠቅሶ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቷል።
ከተከሳሾች መካከል የየካ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር የሰነድ አጣሪ የሕግ ባለሙያ 1ኛ ተከሳሽ አማረ ሞገስ መንግስቱ፣ 2ኛ ተከሳሽ የክፍለ ከተማው የካሳ ግምትና ምትክ ባለሙያ ቢኒያም ደነቀ እና 4ኛ ተከሳሽ የክፍለ ከተማው የመሬት አስተዳደር የካሳ ኦፊሰር ምስጋናው ማሰቦ ይገኙበታል።
በክሱ ላይ ከ1ኛ እስከ 27 ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሶች በየካ ክፍለ ከተማ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተመድበው ሲሰሩ የነበሩ ሲሆን ከ28 እስከ 36ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ደግሞ የአርሶ አደር ኮሚቴ ሳይሆኑ የአርሶ አደር ኮሚቴ ነን በሚል በወረዳ 10 እና ወረዳ 14 በተለያዩ ቦታዎች ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ናቸው ተብሏል፡፡
ከ37ኛ እስከ 48ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾችን በአካባቢው ነዋሪ ሳይሆኑ ነዋሪ ነን በማለት ሀሰተኛ ቃለ ጉባዔ ማቅረባቸው በክሱ ተጠቅሷል።
በአጠቃላይ ከጣፎ እስከ ድንበሯ በሚዘረጋ የከባድ የኤሌክትሪክ መሥመር ዝርጋታ ፕሮጀክት ምክንያት ክፍለ ከተማው የልማት ተነሺዎችን እያስተያናገደ በነበረበት ወቅት ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የክፍለ ከተማው ሠራተኛ ናቸው የተባሉ ከ1ኛ እስከ 27 ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች በህገወጥ መልኩ12 ሚሊየን 882 ሺህ 918 ብር ከ82 ሳንቲም የካሳ ክፍያ እንዲዘጋጅ አድርገዋል ሲል ዐቃቤ ሕግ በክሱ አመላክቷል።
በዚህ መልኩ የልማት ተነሺ ላልሆኑ 10 ግለሰቦች የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ናቸው በሚል ለያንዳንዳቸው 500 ካሬ ሜትር ይዞታ መብት እንዲፈጠርላቸው በማድረግ ጠቅላላ ወቅታዊ የጨረታ ዋጋው 132 ሚሊየን 37 ሺህ 460 ብር ከ82 ሳንቲም የሆነ 4 ሺህ 392 ካሬ ሜትር ይዞታን በሕገ-ወጥ መንገድ በምትክነት እንዲወሰድ በማድረግ በዋና ወንጀል አድራጊነት እና በልዩ ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ሥልጣንን ያለ አግባብ በመገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡
ከተከሳሾች መካከል 2ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ብቻ ችሎት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን በችሎቱ ዳኞች ማንነታቸውን የመለየትና የመመዝገብ ሥራ ተከናውኗል።
ከቀሪ ተከሳሾች መካከል በሌላ የሙስና መዝገብ የተከሰሱና ቀደም ሲል በጊዜ ቀጠሮ ችሎት በዋስ የተፈቱትን ተከሳሾች ጨምሮ 46 ተከሳሾችን የአዲስ አበባ ፖሊስ በቀጣይ ቀጠሮ እንዲያቀርባቸው ታዟል።
ክሱን በችሎት በንባብ ለማሰማት ለፊታችን ሐሙስ ተቀጥሯል።
በታሪክ አዱኛ