አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለመጪዎቹ በዓላት ወቅት እርድ በሚፈፀምበት ጊዜ ለቆዳና ሌጦ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
በእርድ ጊዜ የሚፈጠሩ ጉድለተቶች የቆዳውን ጥራት እንደሚጎዱ ተገልጿል፡፡
በዚህም እንስሳው ሲታረድ ደም ተሟጦ ያለመውጣት፣ የቅርጽ ብልሽት፣ በአሰነዛዘር ወቅት የተፈጥሮ መስመርን ተከትሎ ያለመሰንዘር እና ነጋዴዎችም ቆዳውን ሲሰበስቡ ጥንቃቄ ባለማድረግ በቆዳው ላይ ጉዳት ያደርሳሉ፡፡
በተለይ ከእርድ በኋላ መሬት ላይ መጎተት፣ አንድ ቦታ ላይ ሰብስቦ ማበስበስ፣ ማቆሸሽ፣ መሬት ላይ ማድረቅ እና ሌሎች የቆዳውን ጥራት እንደሚጎዱ ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ለዚህም የቆዳና ሌጦ ጥራት እንዳይጎዳ ለእርድ የሚቀርበውን እንስሳ በዱላ አለመምታት፣ እንስሳው ለእርድ ሲጣል ከመሬት ጋር አለማጋጨት፣ እንስሳው የሚታረድበት ቦታ ንፁህ ማድረግ፣ እንስሳው ሲታረድ ደም ተሟጦ እንዲወጣ ማድረግ፣ ቆዳው ሲገፈፍ ቅርፅን መጠበቅና በአሰነዛዘር ወቅት የተፈጥሮ መስመርን ተከትሎ መሰንዘር ይገባል ተብሏል፡፡
እንዲሁም ቆዳው ሲገፈፍ በቢለዋ እንዳይበሳ መጠንቀቅ፣ ቆዳው ሲሰበሰብ መሬት ላይ አለመጎተት፣ አለማቆሸሽ፣ ቆዳው ሲሰበሰብ እንዳይበሰብስ መጠበቅ፣ መሬት ላይ አለማድረቅና የቆዳና ሌጦ ጥራት እንዳይጎዳ ከሚያደርጉ ዋንኞቹ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ የተትንሳኤ እና ሌሎች በዓላትን ምክንያት በማድረግ እርድ በሚፈፀምበት ጊዜ ከላይ የተጠቀሱና ሌሎች አስፈላጊ ጥንቃቄዎች መደረግ እደሚገባ ተመላክቷል፡፡
በኢትዮጵያ በየዓመቱ በአማካኝ 2 ነጥብ 87 ሚሊየን የቀንድ ከብት ቆዳ፣ 8 ነጥብ 75 ሚሊየን የበግ ሌጦ እና 8 ነጥብ 5 ሚሊየን የፍየል ሌጦ እንደሚመረት መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡