አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በሩሲያ እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ – ሩሲያ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፎረም ላይ የሳይበር ደህንነት ተሞክሮዋን አካፈለች፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ በመድረኩ ÷ ኢትዮጵያ በሳይበር ምህዳሩ ላይ ያለዉን መልካም አጋጣሚ ከመጠቀም ባሻገር የዲጂታል ተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ የዲጂታል ሉዓላዊነት ጥሰትና የሳይበር ጥቃትን ለመቀነስ በራሷ አቅም ቴክኖሎጂዎችን በማበልጸግ ጥቅም ላይ እያዋለች መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገራት የሳይበር ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ላይ ሊሰሩ እንደሚገባ ያነሱት አቶ ሰለሞን፥ በሳይበር ቴክኖሎጂ ላይ ያላቸውን ጥገኝነት በአግባቡ መፈተሽና ማስተካከል ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
ታዳጊ ሃገራት በሌሎች ሀገራት በተለይም ባደጉት ሃገራት ላይ ከፍተኛ የሆነ የቴክኖሎጂ ጥገኝነት ውስጥ በመሆናቸው የዲጂታል ሉዓላዊነታቸዉ ለአደጋ እንዲጋለጥ ማድረጉንም አንስተዋል።
ሀገራት በሳይበር ሉዓላዊነታቸው ላይ ያላቸውን ስጋት ለመቀነስ የራሳቸውን የቴክኖሎጂ ምርቶች መታጠቅና ከዘመኑ ጋር አብሮ መዘመን ይጠበቃል ማለታቸውን ከአስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በይበልጥ እንደ አፍሪካ ያሉ በሳይበር ቴክኖሎጂ ዘርፍ ወደ ኋላ የቀሩ ሀገራት ከፍተኛ የሚባል የዲጂታል ሉዓላዊነት አደጋ እንዳለባቸዉ የጠቆሙት አቶ ሰለሞን፥ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን ማረጋገጥ ካልቻሉ ብሄራዊ ጥቅማቸው ለአደጋ መጋለጡ የማይቀር መሆኑን ጠቁመዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን ሀገራት የሳይበር ምህዳሩ ካለው ድንበር የለሽ ባህሪይ የተነሳ ምህዳሩን ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ ለመጠቀም የጋራ ስታንደርዶችን፣ ፖሊሲዎችን እና የትብብር ማዕቀፎችን በመቅረጽ ሊሰሩ እንደሚገባ በመድረኩ አንስተዋል።