የሀገር ውስጥ ዜና

ምእመኑ በጾም ወቅት ያሳየውን መረዳዳትና አብሮነት የዘወትር ተግባር አድርጎ ሊቀጥል ይገባል-የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ

By Shambel Mihret

April 13, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምእመኑ በጾም ወቅት ያሳየውን መረዳዳትና አብሮነት የዘወትር ተግባር አድርጎ ሊቀጥል እንደሚገባ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የዐቢይ ፆም በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በኩል ደግሞ የረመዳን ወርን በጾምና በጸሎት በማሳለፍ ላይ ይገኛሉ።

የጾም ወቅት ሰው ራሱን ከስጋዊ መሻት አርቆ ለመንፈሳዊነት የሚያስገዛበት ሲሆን÷ በዚህ ወቅት  እንደየሃይማኖቱ አስተምህሮ በጎ ምግባራት የሚከናወኑበትም ነው።

ጾም ፍቅርን በመቸር፣ በጎነትን በተግባር በመግለጥ፣ ያለው ለሌለው በማካፈልና በመተዛዘን የሚፈጸም መንፈሳዊ ተግባር ነው።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ-ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ÷ሃይማኖቶች በጎ ተግባራትና መንፈሳዊ ጸጋ እንደሚያቀዳጁ እነዚህም ዘወትራዊ መሆን እንዳለባቸው ያስተምራሉ ብለዋል።

በጾም ወቅት የነበረው የምእመኑ መረዳዳትና አብሮነት የዘወትር ተግባር ሆኖ ሊቀጥል ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የአባቶችን ምክርና ተግሳፅ በማዳመጥ፣ ከእኩይ ተግባራት በመቆጠብ ምእመኑ መልካምነትን አብዝቶ እንዲያሳይም ጥሪ አቅርበዋል።