አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 7 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶች እና ነዋሪነታቸውን በአሜሪካ ያደረጉ ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፎረም በዋሺንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተካሄደ።
የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ በፎረሙ ላይ እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የኢንቨስትመንት አማራጮች በመጠቀም በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በላይ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተው እንዲሰሩ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል።
በሀገራችን የተጀመረው ዘላቂ ሰላም የማስፈን ሂደት እንዳይቀለበስ በሙሉ ቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በትግበራ ላይ የሚገኘው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የግሉ ዘርፍ ጉልህ ሚና እንዲጫወት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው መንግስት አስቻይ የፖሊሲ ማዕቀፎችን በመዘርጋትና ውስን በሆኑ የኢንቨስትመንት መስኮች ብቻ እንደሚሳተፍ መግለጻቸውን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል።
በተለይም አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ባለሃብቶች ያካበቱትን ሀብት፣ ልምድ እና እውቀት ወደ ሀገራቸው ይዘው በመግባት በግል እና ከሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ጋር በመሆን እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው፥ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ባንኮች የሚሰጡት ብድር ዘጠና በመቶ የሚሆነው ለግል ዘርፉ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለባለሃብቶች ምቹ እንደትሆን ተግባራዊ የፖሊሲ ማሻሻያዎች እንደተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
ባለሃብቶች ከገበያ ዳሰሳ ጥናት፣ ከፈቃድ ማውጣት፣ በስራ ላይ እና ከዛም አልፎ የሚገጥሟቸውን የቢሮክራሲ እና ተያያዥ መሰናክሎች በፍጥነት እልባት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።