አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለጌታችን ለመድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል አደረሳችሁ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አቶ ሽመልስ በዓሉን ስናከብር ሰላምን በማወጅ እና የተጀመረውን የሀገሪቱን የለውጥ ጉዞ ለማሳካት በጋራ በመስራት መሆን አለበትም ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው ÷ ትንሳኤ ክርስቶስ ሞትን በትግስት አሸንፎ የተነሳበት፣ በአዳም ላይ የተፈረደውን ግፍና በደል ሽሮ ፍጹም ደስታና ነጻነት፣ ሰላምና ፍቅር የተገኘበት ነው ብለዋል።
ትንሳኤ መቃብር እና ጨለማ ወደ ዘላለማዊ ብርሃን የተቀየረበት የጽናት፣ የትህትና እና የፍቅር ተምሳሌት ነው ሲሉም አውስተዋል፡፡
ከትንሳኤው ችግርን በትግስት አልፎ ለድል መብቃት እንደሚቻል እንረዳለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ የእኛ ቀዳሚ ደስታ ህዝባችን መሠረታዊ ፍላጎቱ ተሟልቶና ማህበራዊ እረፍት አግኝቶ ማየት ነው ብለዋል።
በተመሳሳይ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ ለትንሳኤ በዓል ባስተላለለፉት መልዕክት÷ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ከሃጽያት ለማንጻት በመስቀል ላይ ውሎ ሞትን ድል በማድረግ ትንሳኤን አብስሯል ብለዋል።
በንግድ ስርዓቱ ላይ የሚስተዋለውን ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ መቆጣጠር እንዲሁም ለወጣት ስራ ፈጣሪዎች የስራ እድል ማመቻቸት እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቅሰዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው÷የክልሉ ህዝበ ክርስቲያን የትንሳዔን በዓል ሲያከብር አብሮነትንና መደጋገፍን በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
በዓሉን ህዝብ ክርስቲያኑ ያለምንም ስጋት እንዲያከብር አስፈለጊው የጸጥታ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)ለበዓሉ ባስተላለፉት መልዕክት÷ በዓሉን ስናከብር በመተሳሰብ፣ በመደጋገፍ፣ የደከመውን በማበርታት፣የተቸገረውን በመርዳት ያለንን በፍቅር በማካፈል ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
ወቅቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነትንና ህብረ ብሔራዊነትን የሚጠይቅ በመሆኑ በዓሉን ስናከብር በፍጹም ኢትዮጵያዊ ባህል እንዲሆንም ጠይቀዋል፡፡
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር÷ትንሳኤ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ፤ በአዳም ላይ የተፈረደውን ሞት በሞቱ ሽሮ፤ ፍጹም ደስታና ነጻነት፣ ሰላምና ፍቅር ለሰዎች የሰጠበት በዓል እንደሆነ ከእምነቱ አስተምህሮ መረዳት ይቻላል ብለዋል።
የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ እንዲሆን ጥሪ ያቀረቡት ከንቲባው÷በዓሉ የሰላም፣ የደስታ፣ የአብሮነት እና የአንድነት እንዲሆንም ተመኝተዋል፡፡