አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2015(ኤፍ ቢ ሲ) ብልጽግና ፓርቲ ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የፓርቲው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለትንሳኤ በአል በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን።
ይህ በአል በህዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ በፆም፣በስግደት እና በምስጋና የሚከበር በንፁህ ህሊና እና አርምሞ ክርስቲያኖች ወደ ፈጣሪያቸው የሚቀርቡበት ታላቅ በአል መሆኑ እጅግ ልዩ እና ደማቅ ያደርገዋል።
በወራት ተደርዘው የነበሩ የምስጋና ቀናት፣በሳምንታት ተከፋፍለው የነበሩ አፇማት፣በቀናት ተቀምረው የነበሩ የስግደት እና የንስሀ ሰአታት በመንፈሳዊ በረከት ምእመናንን ሞልተው እነሆ ትንሳኤ ሊሆን በስቅለቱ ማግስት ላይ ቆመን እንገኛለን።
ኢትዮጵያውያን ከትንሳኤ በአል ጋር ያላቸው ቁርኝት እና በቅድመ በአሉ በመላው ሀገራችን የሚፈጠረው ድባብ በአሉን ተናፋቂ ከማድረጉም በላይ በፆም በስግደት በሚከወኑ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ህብረተሰባችን የሚገነባበት የሞራል ልእልና ቀላል የሚባል አይደለም።
ሰብአዊነትን፣ልግስናን፣ቸርነትን፣ከራስ አልፎ ለሌሎች መኖርን፣ይቅርታን፣ምህረት ማድረግን፣መካፈልን፣ህብረትን፣አንድነት እንዲሁም አርቆ አሳቢነትን ይማራል።
ሀገርን የሞራል ልኬታቸው በዳበረ ዜጎች ለመገንባት የሚያገለግሉ ጡቦች በሙሉ በትንሳኤ ፆም ሰሞን በሚደረጉ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች በምእመናን ዘንድ ይሸመታሉ።ንፁሀን ላይ በትራቸውን የማያነሱ እጆች፣የሀገርን ሀብት ለመመዝበር የማይሰነዘሩ ጣቶች፣ለአመፅ እና ለመጠፋፋት የማይጋበዙ አእምሮዎች፣በሰብአዊነት የተሟሹ ህሊናዎች ይወለዳሉ።
ይህ መሆኑ ደግሞ እንደ አንድ ፖለቲካ ፓርቲ እና ሀገረ መንግስት መሪ ልንገነባት ለምንፈልጋት ሀገር በከፍተኛ ሁኔታ አጋዥ አቅም ነውና በአሉን እና መንፈሳዊ እንቅስቃሴውን በውዴታም ሆነ በግዴታ እንድንጠብቀው የሚያደርገን ምክንያት ሆኖ ሊቀርብ የሚችል ሀቅ ነው።
እንደ ብልፅግና ፓርቲ የትንሳኤ በአልን የመሰሉ ሀይማኖታዊ በአላት ህብረተሰብን ለመገንባት ያላቸውን ሚስጥራዊ ፋይዳ በጥብቅ እንገነዘባለን።ሰው ተኮር በሆነው የፓርቲያችን መርህ ላይ በግልፅ እንደተቀመጠውም ሀይማኖታዊ እና መንፈሳዊ እሴቶችን በአግባቡ በመንከባከብ ለኢትዮጵያ ብልፅግና ተጨማሪ አቅም መፍጠር እንደሚችሉ ያለንን እምነት ገልፀናል።
በአላትን አብሮ በመብላት፣አብሮ በመጠጣት ማእድ እየተጋሩ ማሳለፍ ባህል እንዲሆንም በክቡር የፓርቲያችን ፕሬዝዳንት የተጠነሰሱ በጎ ጅምሮች ተስፋፍተው በርካታ በአላትን በኢትዮጵያዊ የሞራል ልእልና እስከ ታችኛው መዋቅር በሚደርስ የሰብአዊነት ተግባር አሳልፈናል።እያሳለፍንም እንገኛለን።
ይህንን በአልም ስናከብር የተቸገሩ ወገኖቻችን በመርዳት፣አቅመ ደካሞችን በመንከባከብ፣የታረዙትን በማልበስ፣በህግ ጥላ ስር ያሉ ወገኖችን በመጠየቅ፣ቤታቸው የጎደለ ድሆችን አይዟችሁ በማለት፣ካለን እና ቤታችን ካፈራው ላይ በማቋደስ፣ ፍፁም በሆነ መተሳሰብ በሞላው ኢትዮጵያዊ የጨዋነት መንፈስ ሊሆን ይገባል።
ይህን ማድረጋችን አንድም በፈጣሪ ዘንድ ቸሮታን የሚያስገኝልን ሲሆን አንድም ሰብአዊነትን በህብረተሰባችን ዘንድ በማሳደግ የሞራል ልእልናችንን ከፍ የማድረግ አቅም ስላለው ውድ ኢትዮጵያውያን በአሉን በመተሳሰብ እንድታከብሩት አደራ ማለት እንወዳለን።
በበአላት ወቅት መረዳዳት መተሳሰብ እና መደጋገፍ ሰው ተኮር የሆነው የፓርቲያችንን ፖሊሲ እና ስትራቴጂ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያድግ ያስችለዋልና በዚህ በአል ላይ በስፋት በበጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎች መሳተፍ ግድ ይለናል።
መልካምነት ክፍያው ብዙ ነውና፣እንደ ብልፅግናም ልንገነባት የምንፈልጋት ሀገር መሰረቷ ሰብአዊነት ነውና ትኩረታችንን መረዳዳት እና መደጋገፍ ላይ አድርገን በአሉ በሀምራዊነት ተሸምነን የምንንፀባረቅበት፣በቸርነትን እና በልግስና የሚገኘውን በረከት በጋራ የምንቋደስበት ሊሆን ይገባል።
ብልፅግና ፓርቲ
መልካም የትንሳኤ በዓል!!