ዓለምአቀፋዊ ዜና

የአፍሪካ ኅብረት የሠላምና ፀጥታ ም/ቤት በሱዳን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ መከረ

By Alemayehu Geremew

April 16, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ኅብረት የሠላምና ፀጥታው ምክር ቤት በሱዳን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ መከረ፡፡

ጉባዔው የሱዳን ህዝብ በሲቪል መራሽ መንግስት አማካኝነት ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱ ወደ ነበረበት እንዲመለሥ የጠየቀውን ጥያቄ እና ጥረት እንደሚደግፍ ገልጿል፡፡

ለሱዳን ህዝብ ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት፣ ነፃነት እና ፖለቲካዊ አመለካከት መከበር እና ቀጣይነት ያለውን ቁርጠኝነትም አረጋግጧል፡፡

በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች(ልዩ ሃይሎች) መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት እጅግ አሳሳቢ እንደሆነና ወደ ከፍተኛ ግጭት ሊሸጋገር እንደሚችልም ጉባዔው አመላክቶ ዴሞክራሲያዊ እና ሠላማዊ ሽግግር ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት ሊያደናቅፍ ይችላል የሚል ሥጋቱን አስቀምጧል፡፡

በሁለቱ ወገኖች መካከል የተፈጠረው ግጭት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞችን ጨምሮ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ማስከተሉን ጉባዔው ጠቁሞ በጥብቅ አውግዟል፡፡

ለዜጎች ሠላም ሲባል በተለይም ሴቶችን እና ሕፃናትን ለመታደግ ሁለቱ ወገኖች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርቧል።

ሁለቱ ወገኖች ልዩነቶቻቸውን በሰላማዊ እና በሰከነ መንገድ ለመፍታት አካታች እና ሁሉን አቀፍ ውይይት እንዲተገብሩም ጉባዔው ጠይቋል፡፡

ሱዳን ወደ ቀደመ ሰላሟ እንድትመለስ ፣ በሀገሪቷ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲሰፍን እና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ብሎም የሱዳን ህዝብ ፍላጎት እንዲከበር ጠይቋል።

ጉባዔው የሱዳንን ሁኔታ ሊያወሳስብ የሚችል ማንኛውንም የውጭ ጣልቃ-ገብነት እንደሚያወግዝም አስታውቋል፡፡

የቀጣናው ሀገራት እና ባለድርሻ አካላት ሀገሪቷ በሽግግር መንግስት ሂደት ውስጥ ለማለፍ የምታደርገውን ጥረት እንዲደግፉም በጉባዔው ተጠይቋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን በሱዳን ያለውን ግጭት በውይይት እና በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ከሁለቱ ወገኖች ጋር እንዲመክር ጉባዔው ጠይቋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ በሱዳን የጥይት ድምፅ እንዳይሠማ እንዲሠራ ጉባዔው ጥሪ አቅርቧል፡፡

በአፍሪካ ኅብረት፣ በኢጋድ እና በተባበሩት መንግስታት አማካኝነት የሱዳን የፖለቲካ ሽግግር ላይ የሦስትዮሽ ምክክር እንዲቀጥልም ጉባዔው ጠይቋል፡፡

ከትናንት ጀምሮ በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች(ልዩ ሃይሎች) መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት የሰዎችን ሕይወት መቅጠፍ እና የሀገሪቷን ሠላም ማናጋት ጀምሯል፡፡

ይህን ተከትሎ ቀደም ሲል የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግስታት (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በሱዳን የተቀሰቀሰው አለመረጋጋት እንዳሳሰባቸው ጠቁመው ልዩ ጉባዔ እንዲጠራ መጠየቃቸው ይታወቃል፡፡

ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) የኢጋድ አባል ሀገራት መሪዎች እና ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሱዳን የተከሰተው ሁኔታ በአስቸኳይ ይረጋጋ ዘንድ እንዲመክሩም አሳስበዋል፡፡

ለሱዳን እና ለአካባቢው ህዝቦች ጥቅም ሲባል ሀገሪቷ ወደ ቀደመ ሠላሟ መመለስ አለባትም ነው ያሉት፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-