ዓለምአቀፋዊ ዜና

በሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደረሽ ሃይሎች መከካል የተፈጠረው ግጭት መቀጠሉ ተገለጸ

By Mikias Ayele

April 17, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሶስተኛ ቀኑን ያስቆጠረው የሱዳን ጦር እና የሱዳን ፈጥኖ ደረሽ ሃይሎች ግጭት መቀጠሉ ተገልጿል፡፡

ግጭቱ የሱዳን ወታደራዊ መሪ ጄኔራል አብዱል ፈታህ አልቡርሃን በሚመሩት የሱዳን ጦር እና ምክትላቸው በነበሩት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዣዥ መሃመድ ሀምዳን ደጋሎ መካከል የሚደረግ ነው፡፡

አሁን ላይ ሁለቱ ተፋላሚ ሃይሎች በመዲናዋ ካርቱም የሚገኙ ቁልፍ ቦታዎችን ለመቆጣጠር  የተጠናከረ ውጊያ እያደረጉ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በግጭቱ እስካሁን ከ100 በላይ ዜጎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን÷ ከ1 ሺህ 100 በላይ ዜጎች ደግሞ ለጉዳት መዳረጋቸውን የሱዳን ሐኪሞች ማህበር አስታውቋል፡፡

ማህበሩ በካርቱም በሚገኙ ሆስፒታሎች ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ጠቁሞ÷ በግጭቱ ምክንያት የህክምና ግብዓቶችን ለማድረስ  አስቸጋሪ መሆኑን አንስቷል፡፡

ግጭቱ በሀገሪቱ ወታደራዊ አመራሮች ውስጥ ሲደረግ የቆየው የስልጣን ሽኩቻ  አካል የነበረ ሲሆን÷ አሁን ላይ አለመግባባቱ ወደ ግልጽ ግጭት ተሸጋግሯል፡፡

በተለይም 100 ሺህ በላይ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይሎችን ወደ ዋናውየሱዳን  ጦር ለማካተት በተያዘው እቅድ እና አዲሱን ውህድ ሃይል ማን ይመራዋል በሚል የተፈጠረው ውዝግብ ወደ ግጭት ማምራቱ ነው የተገለጸው፡፡