አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት ሕገ ወጡን የፒራሚድ ስልት በሚተገብሩ ድርጅቶች ላይ ሕግ እንዲያስከብር በድርጅቱ ተመልምለው የቆዩ ግለሰቦች ጠየቁ፡፡
“ኢትኬር” የተሰኘው ድርጅት በዚሁ የንግድ ስልት ላይ መሰማራቱን በድርጅቱ ተመልምለው የቆዩ ግለሰቦች አጋልጠዋል።
ጣቢያችን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የደረሰውን ጥቆማ መሰረት በማድረግ÷ በአዲስ አበባ፣ ደሴ እና ጎንደር መረጃ አሰባስቧል።
ግንቦት 5 ቀን 2014 ዓ.ም በ500 ሺህ ብር ካፒታል የተቋቋመው “ኢትኬር” ከዘጠኝ ወራት በኋላ የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም ካፒታሉን ወደ 2 ሚሊየን 867 ሺህ ማሳደጉን የድርጅቱ ሠነዶች ያሳያሉ፡፡
ድርጅቱ የውበት መጠበቂያ ምርቶች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርነት ፈቃድ የተሰጠው መሆኑም ተረጋግጧል፡፡
በድርጅቱ ይሠሩ የነበሩ ግለሰቦች “ኢትኬር” የውበት መጠበቂያ ምርቶች ሽያጭን በሽፋን ቢጠቀምም÷ ሸማችን ሻጭ የሚያደርግ የሽያጭ ስርአት ይከተላል ብለዋል፡፡
ይህም በሸማቾች ጥበቃ አዋጅ 813/2006 ሸማችን ሻጭ የማድረግ ስልትን መከተል ክልክል ነው ተብሎ ከተደነገገውን ጋር የሚጋጭ ተግባር ነው፡፡
መረጃ ሰጭች እንዳሉት÷ የድርጅቱ አሠራር ጥቂቶችን የሚጠቅምና በብዙዎች ላይ ኪሳራ የሚያደርስ ነው፡፡
አማላይ መደለያዎቸን ቢያቀርብም እውነቱ ጥቂቶችን የሚጠቅም መሆኑን ጠቁመው÷ ለአብነትም የመኪና እና የቤት ሽልማት ይሰጣል ይላሉ።
ለጋዜጠኞች ቡድን አባላት ለ “ኢትኬር” አባላት ቤትና መኪና እንደሚሰጥ ተነግሯቸዋል።
የድርጅቱ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ማቲዎስ መባ በበኩላቸው÷ “ኢትኬር” ፒራሚዳዊ ሳይሆን ቀጥተኛ የሽያጭ ስልትን እንደሚጠቀም አስረድተዋል፡፡
“የኢትኬር አስተዋዋቂዎች የሚከፈላቸው ባሻሻጡት ምርት እንጂ በሚያመጡት ሰው አይደለም፣ ንግድ ፈቃድም አላቸው” ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ይሁን እንጅ ከ “ኢትኬር” አባላት ንግድ ፈቃድ እንደማያስፈልግ፣ በመጣው ሰው ልክ እንደሚከፈልና ክፍያውም በዚያው ልክ እየጨመረ እንደሚሄድ፤ ይህም ፒራሚዳዊ አካሄድን የሚያሳይ ስለመሆኑ የፋና ጋዜጠኞች ቡድን በምርመራው አረጋግጧል፡፡
መረጃ ሰጭዎቻችን የንግድ ስልቱ ብዙዎችን ሰለባ እያደረገና እየተስፋፋ ስለሆነ መንግስት ግንዛቤ በመፍጠርና ሕግን በማስከበር ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
በቀጣይ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በጉዳዩ ላይ የመንግስትን አስተያየት የሚያቀርብ ይሆናል፡፡
በፋና የምርመራ ጋዜጠኞች ቡድን
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!