አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ትጥቅ የፈቱ የቀድሞ ተዋጊዎችን የመመዝገብ እና ወደ ማዕከል የማሰባሰብ ሥራ የፊታችን ሰኔ ወር እንደሚጀምር የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አስታወቀ።
መንግሥት የህወሓት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አካል የሆነውን ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ ወደ አንድ ማዕከል የማሰባሰብ እና ሰላማዊ ህይወት እንዲመሩ መልሶ የማቋቋም ሂደት በብሔራዊ ደረጃ ለማካሄድ ወደ ሥራ ገብቷል።
ይህንን መርሐ-ግብር የሚያሳልጥ ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን የተቋቋመ ሲሆን÷ ኮሚሽኑም ሥራውን መጀመር የሚያስችሉ ቅድመ-ዝግጅቶችን እያደረገ ነው ተብሏል።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ÷ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው እንዲመለሱ እና በሀገሪቱ ዘላቂ የሰላም፣ የዴሞክራሲ እና የልማት ሂደት ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የቀድሞ ተዋጊዎች የሚባሉት በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት በነበሩ ግጭቶች እና በሰሜኑ ጦርነት በውጊያ ላይ የነበሩ እና በመንግሥት ኃይሎች ውስጥ የማይታቀፉ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዲሁም ፖለቲካዊ ዓላማቸውን በትጥቅ ለማስፈጸም ሲዋጉ የነበሩ አካላት እንደሚመለከት ጠቁመዋል።
ኮሚሽኑ ሥራ ከጀመረ ሦስት ወራት የተቆጠሩ ሲሆን÷ እስካሁን ኮሚሽኑን የማደራጀት፣ ዓላማውን የማስገንዘብ፣ የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰብ የሚያስችል ውይይት ከለጋሽ እና አጋር አካላት ጋር የማካሄድ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
ከዚህም ባለፈ በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስፈልጉ ቅድመ-ዝግጅቶች መግባባት ላይ መደረሱን ጠቅሰዋል።
በዚህ ሳምንትም ከደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ጋምቤላ ክልል አመራሮች ጋር የቀድሞ ተዋጊዎችን የማቋቋም ሂደትን በሚመለከት የጋራ አቋም ለመያዝ በሐዋሳ ምክክር እንደሚኖር አንሥተዋል።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽኑ የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም ሂደትን በተቀናጀ መንገድ ለማከናወን የሚያስችል የሁለት ዓመት መርሐ-ግብር እና ዕቅድ ማውጣቱንም አምባሳደር ተሾመ ገልጸዋል።
ከተለያዩ የውጭ ሀገራት አምባሳደሮች እና ለጋሽ ተቋማት ጋር በተደረጉ ውይይቶች መንግሥት የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋትን ለማሳካት የጀመረውን ጥረት እንደሚደግፉ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑም መከላከያ ሠራዊቱ እና ሌሎች የፀጥታ ተቋማት የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ አስፈትተው እንደጨረሱ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን ለማስጀመር የሚያስችሉ ተግባራትን በፍጥነት እንደሚያከናውን ጠቅሰዋል።
እስካሁን ባለው መረጃ ከ250 ሺህ እስከ 300 ሺህ የሚደርሱ የቀድሞ ተዋጊዎች በመልሶ የማቋቋም መርሐ-ግብሩ እንደሚካተቱ ጠቅሰው÷ ለዚህም 550 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ ተዋጊዎች ትጥቅ የማስፈታቱ ሥራ መጠናቀቁ እንደተረጋገጠ ወደ አንድ ማዕከል የማሰባሰብ እና የመመዝገብ ሥራ በመጪው ሰኔ 2015 ዓ.ም ይጀመራል ብለዋል።
ምዝገባው በኤሌክትሮኒክስ ታግዞ የሚከናወን ሲሆን÷ ለዚህም አስፈላጊ የሶፍትዌር እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን የማልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል።
የቀድሞ ተዋጊዎች፣ ስም፣ የመኖሪያ አድራሻ፣ የሥራ ሁኔታ፣ የጤና፣ የትምህርት እና ሌሎችም ዝርዝር ጉዳዮች በምዝገባው እንደሚካተቱም ጠቁመዋል።
ከምዝገባው ጎን ለጎን የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ማዕከላት የማሰባሰብ ሂደቱን ለማሳለጥም ከወዲሁ በየክልሎች ያሉ ማዕከላትን የሚገመግም ቡድን ተቋቁሞ እየሠራ እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከሎጂስቲክስ፣ ከማኅበራዊ አገልግሎት እና ከፀጥታ ሁኔታ አንጻርም ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመገምገም ከመከላከያና ከክልሎች ጋር እንደሚሠራ ተናግረዋል።