የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ እስላማዊ ቅርሶች በቀጠናው የባህልና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር ያስችላሉ – ሱዳናዊ የቀድሞ ዲፕሎማት

By Alemayehu Geremew

April 19, 2023

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 11 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እስላማዊ ቅርሶች በቀጠናው የባህልና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር እንደሚያስችሉ ሱዳናዊው የቀድሞ ዲፕሎማት፣ የፖለቲካ ተንታኝ እና ጋዜጠኛ መኪ ኤልሞግራቢ ተናገሩ።

ኤልሞግራቢ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ ቀደምት የእስልምና እምነት ተከታዮች ከመካ መዲና ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው በእስልምና እምነት ታሪክ ውስጥ ዋነኛው ሁነት መሆኑን አንስተዋል።

በመካ የነበሩ ሙስሊሞች ያጋጠማቸውን እንግልት ተከትሎም ነብዩ መሐመድ ምዕመኑ ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ እንዲጠለሉ ምክር እንደሰጧቸው አስታውሰዋል።

ይህ ሁኔታም ኢትዮጵያ በመላው ዓለም በሚገኙ ሙስሊሞች ዘንድ ልዩ ቦታ እንድታገኝ አስችሏታልም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ጥንታዊ መስጊዶችን ጨምሮ፥ የቅዱስ ቁርአን፣ መድረሳ እና መንዙማዎችን እና የተለያዩ እስልምናን የሚገልጹ ቅርሶች እንዳሏትም አስረድተዋል።

አያይዘውም “በእነዚህ ሃይማኖታዊ ቅርሶች ላይ የማስተዋወቅ ስራ ቢሰራ የቀጠናውን ብሎም የአህጉሪቱን ባህላዊና ማህበራዊ ትስስር ለማጠናከር” ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

ከእነዚህ መካከልም በ7ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተገነባ እና በአፍሪካ የመጀመሪያ እንደሆነ የሚነገርለትን የአል ነጃሺ መስጊድን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ታሪካዊቷ የሐረር ከተማ በእሥልምና አስተምህሮ ከፍተኛ ክብር የሚሰጣት አራተኛዋ ከተማ መሆኗን አንስተዋል፡፡

ምንም እንኳን ከተማዋ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበች ቢሆንም በአፍሪካ እና በመላው ዓለም ሙስሊም ማኅበረሰብ ዘንድ መታወቅ ባለባት ልክ አልታወቀችም ሲሉም ያነሳሉ፡፡

በመሆኑም በመላው ዓለም ለሚገኙ ሙስሊሞች የሐረርን ባሕላዊ እና ማኅበራዊ ትሥሥር ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ ማስተዋወቅ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡

ምኅዳሩ ቢመቻች በመላው ዓለም የሚገኙ ሙስሊም ጎብኚዎች ስለ ኢትዮጵያ ኢሥላማዊ ቅርሶች ይበልጥ ማወቅ እንደሚሹ አመላክተዋል፡፡

ይህን በማድረግ የሀገሪቷን የቱሪዝም ዘርፍ በሌላ ተጨማሪ አቅጣጫ ማሳደግ እንደሚቻልም ያላቸውን ምልከታ ጠቁመዋል፡፡

ሙስሊም ጎብኚዎችን ትኩረት ያደረጉ ልዩ መርሐ ግብሮች በማዘጋጀት የቱሪዝሙን ዘርፍ የበለጠ ማነቃቃት እንደሚቻል ይገልጻሉ፡፡

አፍሪካውያን በኢትዮጵያ ስላለው ኢሥላማዊ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ሥፍራዎች የበለጠ እንዲያውቁ መንግስት እና ባለድርሻ አካላትኃላፊነት አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሙስሊምና ክርስቲያኑ አብሮ ባሕሉን እና ሃይማኖቱን የሚያከብርበት ሀገር መሆኗን ማየታቸውን እና ክርስቲያኖች ከሙስሊም ጓደኞቻቸው ጋር ሲያፈጥሩ መመልከታቸውን መስክረዋል፡፡

የሠላም ሥምምነቱ እና የአተገባበር ሂደቱ እስልምናን በኢትዮጵያ ይበልጥ ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ እንደሆነም መኪ ኤልሞግራቢ ጨምረው ገልጸዋል፡፡