አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2015 ዓ.ም የዒድ አልፈጥር በዓል ጨረቃ ሐሙስ ማታ ከታየች ዓርብ፣ ካልታየች ደግሞ ቅዳሜ እንደሚከበር የፌዴራል ጠቅላይ ሼሪዓ ፍርድ ቤት አስታውቋል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ሼሪዓ ፍርድ ቤት የ2015ዓ.ም የዒድ አልፈጥር በዓል አከባበርን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
በመግለጫውም÷ ለእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ለ1 ሺህ 444ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል ዋዜማ እንኳን በሳላም አደረሳችሁ ብሏል፡፡
በዓሉ ለኢትዮጵያና ለመላው ዓለም ሕዝብ÷የሰላም፣ የደስታና የፍቅር እንዲሆንም መልካም ምኞቱን ገልጿል፡፡
የዘንድሮው የዒድ አልፈጥር በዓል ጨረቃ ሐሙስ ማታ ከታየች ዓርብ፤ ካልታየች ደግሞ ቅዳሜ እንደሚከበር ነው ፍርድ ቤቱ ያስታወቀው፡፡
በተመሳሳይ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዒድ አልፈጥር በዓልን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ÷ በዓሉ የሰላም፣ የደስታ፣ የመተዛዘን እና የመረዳዳት እንዲሆን የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሸህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ÷ የረመዷን ወርን አስመልክቶ በተለያዩ ከተሞች የተካሄዱ የጎዳ ላይ ኢፍጣር መርሐ ግብሮች ሰላማዊ ሆነው እንዲጠናቀቁ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
በታላቁ የረመዷን ወር መጨረሻ የሚከበረውን የዒድ አልፈጥር በዓልን በሰላምና በመተሳሰብ እንዲሁም የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ማሳለፍ እንደሚገባም ፕሬዚዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በፈቲያ አብደላ እና ብርሃን ደሳለኝ