አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 1 ሺህ 444ኛው የዒድ አልፈጥር ረመዳን በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሐይል አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቋል፡፡
የበዓሉ የኢድ ሶላት ተጀምሮ እሰከሚጠናቀቅ የሚዘጉ መንገዶች እንደሚኖሩም የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በየዓመቱ ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት አንዱ የሆነው የዒድ አልፈጥር ረመዳን በዓል በመላው የእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ በዓል መሆኑን የጋራ ግብረ ሃይሉ ገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ስታዲዮምና በዙሪያው የሚከናወነው የዒድ ሶላት ላይ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች የሚታደሙበት እንደመሆኑ የሶላት ስነ-ስርዓቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ እና የበዓሉ ድባብ ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ወቅታዊውን የፀጥታ ሁኔታ ያገናዘበ ዕቅድ አውጥቶ ወደ ስራ መግባቱን የጋራ ግብረ ሐይሉ አስታውቋል፡፡
የዕምነቱ ተከታዮችና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በተለይም ለኢድ ሶላት የሚመጣውን ህዝበ ሙስሊም በማስተባበር እና የበዓሉን ድባብ ሊያደፈርስ የሚችል ችግር እንዳያጋጥም ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው በመስራት የሚያደርጉት ተሳትፎ የጎላ መሆኑንም የጋራ ግብሩ ሃይሉ ጠቅሷል፡፡
በዘንድሮው በዓልም ይህንኑ አጠናክሮ ለማስቀጠል ከዕምነቱ አባቶች እና ከወጣቶች ጋር ተገቢው ውይይት መደረጉ ነው የተመላከተው፡፡፡
የዕምነቱ ተከታዮች በየአካባቢያቸው በዓሉን ሲያከብሩም ሆነ ወደ ዒድ ሶላቱ ሲመጡ እንደወትሮው ሁሉ የፖሊስን መስተንግዶና ትዕዛዝ በማክበር ተባባሪ እንዲሆኑ እና የበዓሉ ስነ ስርዓት በሰላም እንዲጠናቀቅ መላው የከተማችን ነዋሪዎች የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉ የጋራ ግብረ ሐይሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በዚህ ህብረተሰቡ ለሰላም እንቅፋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት በ011-1-26-43-59 ፣ 011-5-52-63-02/03፣ 011-5-52-40-77፣ 011-5-54-36-78 እና 011-5-54-36-81 እንዲሁም በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች ጥቆማ በመስጠትና አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የጋራ ግብረ ሃይሉ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
በተጨማሪም የዒድ አልፈጥር ረመዳን በዓል የኢድ ሶላት ተጀምሮ እሰከሚጠናቀቅ ለተሸከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶች እንደሚኖሩ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር አሽከርካሪዎች ከዚህ በታች የተገለፁት መንገዶች ዝግ መሆናቸውን ተገንዝበው ሌሎች አማራጮችን እንዲጠቀሙም አሳስቧል፡፡
በዚህም መሰረት
– ከቦሌ አየር መንገድ በሚሊኒየም አዳራሽ ወደ ስታዲዮም የሚወስደው መንገድ ደንበል ሲቲ ሴንተር ኦሎምፒያ አደባባይ አከባቢ
– ከመገናኛ ፣ በሃያ ሁለት ወደ መስቀል አደባባይ እንዲሁም ከቦሌ መድሃኒያለም፣ በአትላስ ሆቴል ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ኡራኤል ቤተ-ክርስቲያን አካባቢ
– ከአራት ኪሎ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ባሻ ወልዴ ችሎት ወይም ፓርላማ መብራት
– ከፒያሣ አካባቢ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ቸርችል ጎዳና ቴዎድሮስ አደባባይ
– ከተክለ ሀይማኖት በሜትሮሎጂ ወደ ስታዲዮም የሚወስደው መንገድ ሜትሮሎጂ መስሪያ ቤት አካባቢ
– ከተክለ ሀይማኖት ፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሚወስደው መንገድ ጥቁር አንበሳ የኋላ በር አካባቢ
– ከሲኒማ ራስ በጎላ ሚካኤል ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ጎላ ሚካኤል መስቀኛ
– ከጌጃ ሰፈር ፣ ጤና ጥበቃ፣ ብሄራዊ ቲያትር የሚወስደው መንገድ ጎማ ቁጠባ
– ከባሻ ወልዴ ችሎት በኦርማ ጋራዥ ወደ ፍል ውሃ መስኪድ የሚወስደው መንገድ ንግድ ማተሚያ ቤት
– ከጎፋ በቅዱስ ቂርቆስ ቤ/ክ ወደ ለገሐር አዲሱ መንገድ የሚወስደው መንገድ ቅዱስ ቂርቆስ ቤ/ክ መስቀለኛው ላይ
– ከጦር ኃይሎች ፣ ልደታ ፣ ፖሊስ ሆስፒታል ሜክሲኮ አደባባይ
– ከሳሪስ በጎተራ ወደ መስቀል አደባባይ ለቀላል መኪና የቀድሞ አራተኛ ክፍለ ጦር አካባቢ እንዲሁም ለከባድ መኪና አጎና ሲኒማ አካባቢ
ይለፍ ለሌላቸው ተሽከርካሪዎች ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ ዝግጅቱ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ዝግ በመሆኑም ህብረተሰቡ ከፖሊስ የተሰጠውን መረጃ ተገንዝቦ የትራፊክ ፖሊስ አባላት በሚጠቁሙት አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀም እና ለትራፊክ ፖሊስ አባላት ትዕዛዝ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ለእምነቱ ተከታዮች በዓሉ በሙሉ በዓሉ የፍቅርና የሰላም እንዲሆን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሐይል መልካም ምኞቱን ገልጿል፡፡