የሀገር ውስጥ ዜና

ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራን ስርዓት ለማስያዝ በትኩረት እየተሠራ ነው – አቶ አሻድሊ ሀሰን

By Shambel Mihret

April 20, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚስተዋለውን ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ ስርዓት ለማስያዝ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ የሚስተዋለውን ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ መልክ ለማስያዝ ከተቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴ ጋር እስካሁን የተሠሩ ሥራዎችን ገምግመዋል።

በመድረኩ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል የተለየ የክትትልና የቁጥጥር ሥራ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አቶ አሻድሊ ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት በቀጣይ በሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ ላይ በሚሣተፉ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ይወስዳልም ነው ያሉት፡፡

ኮሚቴው ባለፉት ወራት ያከናወናቸውን ሥራዎች በመገምገም የቀጣይ አቅጣጫ ማስቀመጡንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡