የሀገር ውስጥ ዜና

የፋሲካ በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በመከበር ላይ ይገኛል

By Tibebu Kebede

April 19, 2020

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2012( ኤፍ.ቢ.ሲ) የፋሲካ በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በመከበር ላይ ይገኛል።

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የሁሉም የክርስትና አምነት ተከታዮች ከወትሮው በተለየ መልኩ ምሽቱን በየመኖሪያ ቤታቸው ፋሲካን ተቀብለዋል።

ለሊቱን የተለያዩ እምነት ተከታዮችም በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከተለያዩ የክርስትና እምነት ተቋማት ቀጥታ ሲተላለፉ የነበሩ ቅዳሴ እና ሌሎች ሐይማኖታዊ ስነ ስርዓቶችን ከቤታቸው በመከታተል በዓሉን ተቀብለዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በሀገሪቱ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሐይማኖታዊ ስነ ስርዓት እና ለተለያዩ ማህበራዊ ጉዳይ መሰባሰብን ከልክሏል።

ይንንም ተከትሎ የዘንድሮው የፋሲካ በዓል በተለየ ድባብ ውስጥ ዕየተከበረ ይገኛል።

የክርስትና ሀይማኖት አባቶም ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፥ በመላ አገሪቱ ለገጠርና ለከተማ፣ ከአገር ውጪ፣ የአገሪቷን ዳር ድንበር እየጠበቁ ለሚገኙና በሕመም ላይ ላሉ እንዲሁም ለሕግ ታራሚዎች እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ “የዘንድሮው በዓላችን በሃዘንና በጨለማ የተከበበ ቢመስለንም በተስፋ የተሞላን ሆነን እናከብረዋለን” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ እየሱስ ፕሬዚዳንት ቄስ ዮናስ ይገዙ በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ ክስተት አድማሱን እያሰፋና ጥቃት እያደረሰ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት  ሁሉም ዜጋ ራሱን በመጠበቅ ለወገኑ መጠንቀቅና ከመንግስት፣ ከባከሙያዎችና ከሀይማኖት መሪዎች የሚሰጠውን ምክር ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅበት በመልካም በዓል መልዕክታቸው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዝዳንት ፓስተር ጻድቁ  አብዶ  በመልዕክታቸው “ትንሳኤው ብርሃን ጨለማን ያሸነፈበት፣ ሞት ድል የተነሳበት፣ ሀሰት ተንኮል ጥላቻ በፍቅርና በዕውነት የተረቱበት፤ ብርሃን ህይወትና ፍቅር ርህራሄ አሸንፈው እና ድል ነስተው ዘመነ ፍዳ በዘመነ ምህረት የተለወጠበት ትንሳዔ ነው”ብለዋል፡፡