የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የምግብ ፖሊሲ ምርምር ተቋምጋር ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ፈረመች

By Shambel Mihret

April 24, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፍ የምግብ ፖሊሲ ምርምር ተቋም ጋር በትብብር ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።

ስምምነቱን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) እና መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የዓለም አቀፉ የምግብ ፖሊሲ ምርምር ተቋም (አይኤፍፒአርአይ) ዳይሬክተር ጆን ስዊነን ፈርመውታል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱ ሚኒስቴሩ ከተቋሙ ጋር በአቅም ግንባታ እና የዕውቀት ሽግግርን ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ምርምሮችን በጋራ ለማከናወን የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ከመስኖ ልማት ጋር በተያያዘ በውኃ ላይ ያተኮሩ የፖሊሲ ምርምሮችን እንዲሁም በቆላማ አካባቢዎች መስኖን መሠረት ያደረጉ ምርምሮችን ማካሄድንም ይጨምራል ነው የተባለው።

በተለይም በመስኖ ልማት ዕድሎችና ተግዳሮቶች በመለየት የመስኖ ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋፋትና ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች በጋራ ለመሥራት የሚያስችል መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።