አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአፍሪካውያን ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ለሚለው አህጉራዊ መርህ ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን የፈታችበት መንገድ ሁነኛ ተምሳሌት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ፡፡
አምባሳደር ምስጋኑ ከአፍሪካ ሕብረት የፖለቲካ፣ የሰላም እና ደኅንነት ጉዳዮች ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬ ጋር መክረዋል፡፡
በውይይታቸው አምባሳደር ምስጋኑ በኢትዮጵያ ለመጣው ሰላም የአፍሪካ ሕብረት ያደረገውን ድጋፍ አድንቀው÷ በአፍሪካ የሚከሰቱ ችግሮችን በራስ አቅም የመፍታትን መተማመን ያሳየ ነው ብለዋል ።
የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰዳቸው እርምጃዎች የአፍሪካ ሕብረት ታሪካዊ ኃላፊነት እንዲወጣ ያስቻለ አጋጣሚ እንደነበርም ነው ያስገነዘቡት፡፡
በዚህም አባል ሀገራት እና የአፍሪካ ሕብረት አጋሮች ለተቋሙ ያላቸው እምነት እንዲጠንክር አስችሏል ነው ያሉት ።
አምባሳደር ምስጋኑ የፓን አፍሪካ ዕሴቶች እንዲጠናከሩ በአፍሪካ ወደፊት የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ዘዴ በማጎልበት ኢትዮጵያ እንደምሳሌ የምትወሰድ ሀገር መሆኗን አስረድተዋል፡፡
በማንኛውም የሰላም ውይይቶች የአፍሪካ ሕብረት ሐሳብ የሚታይበት ማዕቀፍ እንዲሰፋ መሥራት እንደሚገባ ሚኒስትር ዴኤታው መግለፃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
አምባሳደር ምስጋኑ ሱዳናውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው የመፍታት አቅም እንዳላቸውም ነው ያመላከቱት፡፡
በተፈጠረው ችግር ምክንያት ከካርቱም እና ከሌሎች አካባቢዎች ያሉ የውጭ ሀገራት ዜጎችን ለማገዝ ግብረኃይል ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬ በበኩላቸው÷ የአፍሪካን ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሀገራት የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ለወሰዳቸው እርምጃዎች ትልቅ አክብሮት እንዳላቸውም ነው የገለጹት፡፡
የሽግግር ፍትሕ እንዲፈፀም በመንግሥት በኩል የሚደረገውን ጥረት የአፍሪካ ሕብረት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።