የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ እና ኮሞሮስ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል የሚያስችል ስምምነት ፈረሙ

By ዮሐንስ ደርበው

April 25, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እና ኮሞሮስ መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማሻሻል የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ፡፡

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአራት የአፍሪካ ሀገራት የሚያደርጉትን ጉብኝት በመቀጠል ዛሬ ኮሞሮስ መዲና ሜሮኒ መግባታቸው ይታወቃል፡፡

አቶ ደመቀ ከወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ከሆኑት የኮሞሮስ ፕሬዚዳንት አዛሊ ጋር ባደረጉት ውይይት÷ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አተገባበር ላይ ገለፃ አድርገዋል።

ፕሬዚዳንት አዛሊ የወቅቱ የሕብረቱ ሊቀመንበር በመሆናቸው የታላቁ የህዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ውይይት ውጤታማ እንዲሆን የመሪነት ሚና እንዳላቸው አቶ ደመቀ አስገንዝበዋል፡፡

ፕሬዚዳንት አዛሊ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም በመስፈኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

የሁለትዮሽ ትብብሩ በግብርና እና አሳ ልማት መስኮች መጠናከር እንደሚችል ማመላከታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

በህዳሴ ግድብ ላይ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና እና ግብፅ መካከል የሦስትዮሽ ድርድሩ እንዲቀጥል እንደሚሠሩም አረጋግጠዋል፡፡

የሱዳን የፀጥታ ሁኔታ በውይይት እንዲፈታም ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ ደመቀ የጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይ አሕመድን መልዕክት ለፕሬዚዳንቱ አድርሰዋል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!