የሀገር ውስጥ ዜና

የተሻሻለው የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ ጸደቀ

By Alemayehu Geremew

April 25, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሻሻለውን የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ ዛሬ አጽድቋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ጉባዔውን ዛሬ አካሂዷል፡፡

አዋጁ÷ የመከላከያ ሰራዊት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ ሀገርን የመጠበቅ ተልዕኮውን በአግባቡ እንዲወጣ ማድረግ የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎች እንደተካተቱበት ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም አዋጁ ኅብረ ብሔራዊ ተዋፅኦውን የጠበቀ የዘመነ ሰራዊት ለመገንባት ማነቆ የሆኑ የሕግ ማዕቀፎችን ማሻሻል እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡

ተሻሽሎ የቀረበው አዋጅ ያሉትን ችግሮችና ክፍተቶች በመሙላት ሊያሠራ የሚችል የሕግ ማዕቀፍ፣ አደረጃጀት እና አሠራር ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑን በማመን ምክር ቤቱ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

የመከላከያ ሠራዊቱን የሚመጥን ራሱን የቻለ የመከላከያ አዋጅ ሊወጣ እንደሚገባ ቀደም ሲል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሲጠየቅ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ለመከላከያ ሠራዊት ክብር የሚመጥን የደመወዝና የካሳ ክፍያ እንዲሁም ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች በሚገባ እንዲከበሩ ራሱን ችሎ የመከላከያ አዋጅ ቢወጣ የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረውም ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

ከጡረታ መውጫ ዕድሜ ጣሪያ አወሳሰንና የጡረታ ዕድሜ ከማራዘም ጋር በተገናኘ፣ ከሠራዊት መብትና ጥቅማ ጥቅሞች አንጻር መታየት ያለባቸውን ጉዳዮች በአዋጅ ማሻሻያው እንዲካተቱ ትኩረት ከተሰጠባቸው ጉዳዮች መካከል ናቸው፡፡

የሀገርን ኅልውናን አደጋ ላይ የሚጥል ጦርነት ሲከሰት የሠራዊት አባል የነበሩትን መልሶ ከመቅጠር ጋር በተገናኘ ስለሚኖረው አፈጻጸም፣ ስለ ብሔራዊ አገልግሎትና ሌሎች የአፈጻጸም ክፍተት ያለባቸውን ጉዳዮች ለማስተካከል የአዋጁ መሻሻል አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱም ታምኖበታል፡፡