የሀገር ውስጥ ዜና

የኩላሊት ታማሚ የተኛ በማስመሰል በህክምና ሰበብ ገንዘብ ሲሰበስቡ የተገኙ 4 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

By Feven Bishaw

April 25, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ”ሚኒባስ” ተሽከርካሪ ውስጥ ባዶ ፍራሽ አንጥፈው የኩላሊት ታማሚ የተኛ በማስመሰል በሕክምና ሰበብ ገንዘብ ሲሰበስቡ የተገኙ አራት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ግለሰቦቹ የማታለል ድርጊቱን ሲፈፅሙ የተገኙት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ሲኒማራስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በ”ሚኒባስ” ተሽከርካሪ ውስጥ ባዶ ፍራሽ በማንጠፍ ፣ በፍራሹ ላይ የኩላሊት በሽታ ታማሚ የተኛ በማስመሰል እና የግለሰብ ፎቶ በባነር አሳትመው በመስቀል እየቀሰቀሱ በህክምና ወጪ ሰበብ ከህብረተሰቡ ገንዘብ ሲሰበስቡ መገኘታቸው ተመላክቷል፡፡

የፖሊስ አባላት ድርጊቱን ተጠራጥረው ባከናወኑት የማረጋገጥ ስራ አራቱም ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተጠቅሷል፡፡

መደጋገፍና መረዳዳት መልካም ቢሆንም በአቋራጭ ለመበልፀግ ህብረተሰቡን በማታለል እንዲህ አይነት ህገ ወጥ ተግባር የሚፈፅሙ ግለሰቦች መኖራቸውን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ፖሊስ አሳስቧል፡፡

በዚህም እውነተኛ ድጋፍ የሚፈልጉ ሰዎችን ማገዝ እንደተጠበቀ ሆኖ በሕክምና ሰነዶች እና በሌሎች ሁኔታዎች የማረጋገጥ ስራ በመስራት አታላዮችን ማጋለጥ እንደሚገባ መልዕክት መተላለፉን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡