የሀገር ውስጥ ዜና

አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከሩሲያ-አፍሪካ አጋርነት ፎረም ሴክሬታሪያት ኃላፊ ጋር ተወያዩ

By Amele Demsew

April 25, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የሩሲያ-አፍሪካ አጋርነት ፎረም ሴክሬታሪያት ኃላፊ አምባሳደር ኦሌግ ኦዜሮቭን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

በውይይታቸውም÷አምባሳደር ምስጋኑ ኢትዮጵያ አስቸጋሪ ጊዜ ባሳለፈችበት ወቅት የሩሲያ ህዝብ ላሳየው አጋርነት በኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ እና የሩሲያን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝነትም ለአምባሳደር ኦሌግ ኦዜሮቭ ገልጸዋል፡፡

አምባሳደር ምስጋኑ በኢትዮጵያ አዲስ የሰላም ዘመን ያበሰረውን “ጦርነት ይብቃ ሰላምን እናጽና” የሰላም ሂደት ስላደረጉት ገንቢ አስተዋጽኦ አምባሳደር ኦዜሮቭን አመስግነዋል።

በሀገሪቱ የተገኘውን ሰላምና መረጋጋት አጠናክሮ በመቀጠል ልማት እና ድህነት ቅነሳ ላይ መስራት የኢትዮጵያ መንግስት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው።

አምባሳደር ኦዜሮቭ በበኩላቸው÷በፈረንጆች አቆጣጠር ከሐምሌ 25 እስከ 30 ቀን 2023 በሩሲያ ፌደሬሽን ስለሚካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ዝግጅት ለአምባሳደር ምስጋኑ አብራርተዋል፡፡

ሩሲያ በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ያመጣውን “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለውን መርህ እንደምትደግፍም አምባሳደር ኦዜሮቭ ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡