አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም አእምሯዊ ንብረት ቀን “ሴቶችና አዕምሯዊ ንብረት፤ ኢኖቬሽንና ፈጠራን ማፋጠን” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል፡፡
በየዓመቱ ሚያዚያ 18 ቀን የሚከበረው የዓለም አእምሯዊ ንብረት ቀን በሳይንስ ሙዚዬም በፓናል ውይይት እና የፈጠራ ስራዎች ዓውደ ርዕይ ነው የተከበረው።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋየ (ዶ/ር) ÷ ሴት የፈጠራ ባለሙያዎች የአእምሮ ስራዎቻቸው በቂ የሕግ ጥበቃ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪም ጥቅም ላይ የሚውልበትን ሁኔታ ማመቻቸት እና ጥረታቸውን ማበረታታት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ኢኖቬሽንና ፈጠራን ከማሳደግ አኳያ የሴቶችን ሚናና ድርሻ ከግምት ውስጥ ያስገቡ ተግባራትን በትብብር መንፈስና በቅንጅት መስራት አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሁሪያ አሊ በበኩላቸው÷ ሴቶች አቅማቸውን እንዲጠቀሙ እና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ሊገድቡ የሚችሉ ተግዳቶሮችን መቅረፍ ይገባል ብለዋል፡፡
የሴቶችን የፈጠራ አቅም መጨመርና ስራዎቻቸውን በአእምሯዊ ንብረት በማስመዝገብ ማበረታታት ይገባል ያሉት ደግሞ÷የቀድሞ የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) ናቸው፡፡
የዓለም አእምሯዊ ንብረት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ21ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ20 ኛ ጊዜ ነው የተከበረው።
በዘመን በየነ