አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጀርመን የልማት ኤጄንሲ (ጂ.አይ.ዜድ) የተቀናጁ አግሮ ኢንዱስትሪያል ፓርኮችን እና አምራች ዘርፎችን አቅም በማሳደግ የበለጠ ለመጠቀም ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ከጀርመን የልማት ኤጄንሲ (ጂ.አይ.ዜድ) ማኔጅመንት የቦርድ ሰብሳቢ ቶርስተን ሻፈር ጉምበል ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ወ/ሮ ሰመሪታ በውይይታቸው ላይ የተወሰኑ ኢኮኖሚያዊ ሴክተሮችን በከፊል ወደ ግል ለማዞር በተደረገ ጥረት ስኬት መመዝገቡን አስረድተዋል፡፡
ጂ.አይ.ዜድ የተቀናጁ አግሮ ኢንዱስትሪያል ፓርኮችን ጨምሮ ሌሎች አምራች ዘርፎችን በማልማት አቅማቸውን በማሳደግ የበለጠ ለመጠቀም እንዲቻል ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቃቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ልዑኩ የሐዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክን መጎብኘቱን ጠቁመው÷ በፓርኩ እየተመረቱ ያሉ ጥሬ ዕቃዎች ጥራት የሚደነቅ እና ተስፋ የሚጣልበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሁለቱም ወገኖች የልማት ትብብርን የበለጠ ለማጠናከር፣ የነባር ፕሮጀክቶችን አጠቃላይ አፈፃፀም ለማሻሻል እና በቀጣይ በቅንጅት ለመሥራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
ጂ.አይ.ዜድ በጀርመን ኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ሚኒስቴር ሥር የሚገኝ የጀርመን ልማት ኤጀንሲ ነው፡፡