የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ አየር መንገድን የሚመጥን የአቪዬሽን ደህንነት ዘርፍ የማሻሻያ ስራዎች መካሄዱ ተገለጸ

By Amele Demsew

April 29, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎትና ተደራሽነት የሚመጥን የአቪዬሽን ደህንነት ዘርፉን ለማጠናከር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

አገልግሎቱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መረጃ ፥ በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ስር የሚገኘውና እንደ አዲስ የተደራጀው የሲቪል አቪዬሽን ደህንነት ዋና መምሪያ የሪፎርም ሥራዎች በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎችና በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፍተኛ የሥራ አመራሮች ተጎብኝቷል።

በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት ዳይሬክተር ጄኔራል ተመስገን ጥሩነህ እንደገለጹት፥ አገልግሎቱ መሥሪያ ቤቱ ከአቪዬሽን ደህንነት ጋር በተያያዘ የሚታዩ ውስንነቶችን በተመለከተ ሰፊ ጥናት አድርጓል፡፡

በዚህ ጥናት መነሻነትም የአቪዬሽን ደኅንነት አገልግሎት ሥራዎች ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ እንዲታጠቁ ፤ ዘርፉን በሰው ኃይል ለማጠናከር እንዲሁም ደህንነቱ የተጠበቀ ቀልጣፋ የደህንነት አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻል የሲቪል አቪዬሽን ደህንነት ዋና መምሪያ በአዲስ መልክ ተደራጅቷልም ብለዋል፡፡

የሀገር መልካም ገጽታ ምልክት የሆነውንና እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎትና ተደራሽነት በሚመጥን መልኩ የአቪዬሽን ደህንነት ዘርፍ ሥራን ለማዘመን በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ነው ያብራሩት።

የአቪዬሽን ደህንነት ዘርፍ የአንድ የተወሰነ አካል ሥራ ብቻ ባለመሆኑ ቀደም ሲል በተደረገው ጥናት የተለዩ እጥረቶች ላይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ያከናወኗቸው ማስተካከያዎችን በተመለከተ የደህንነትና የለውጥ ሥራ ኦዲት ማከናወን እንደሚገባም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው ፥ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ለአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፍ የተሰጠውን ትኩረት ተከትሎ በኤርፖርቶች ያለው የደህንነት ሁኔታ ከመቼውም ጊዜ በላይ የተሻለና በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ የሚገኝ መሆኑን ተናግረዋል።

አዲስ አበባ በጂኦ-ፖለቲካ አቀማመጧ የተነሳ ለደኅንነት ስጋት ተጋላጭ ብትሆንም በዘርፉ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በኩል በመናበብና በቅንጅት የመሥራት ባህል በመዳበሩና በተሰጠው ልዩ ትኩረት እስካሁን አደጋ እንዳላጋጠመም ነው ያነሱት።

በጉብኝቱም ፥ የአቪዬሽን ደህንነት ዘርፍ በአደረጃጀት፣ በአሰራር ስርዓት፣ በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ ጥሩ አቋም ላይ እንደደረሰ መመልከታቸውን ጠቅሰውዋል፡፡

ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አየር መንገዱ የበኩሉን አስተዋፅዖ እና ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የአቪዬሽን ደህንነት ቁልፍ ከሚባሉ ሀገራዊ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ያመለከቱት ደግሞ በጉብኝት መርሐግብሩ የታደሙት የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር) ናቸው፡፡

ዘርፉ ከደኅንነት አንፃር ብቻ ሳይሆን በሀገር ኢኮኖሚ፣ ገጽታና ሌሎች መስኮች የሚያመጣውን ሁለንተናዊ ተጽዕኖ ታሳቢ ያደረገና ወደፊት አንድ እርምጃ የተራመደ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን መመልከታቸውን ተናግረዋል።

የአቪዬሽን ደህንነት በተሟላ መንገድ እየተረጋገጠ ደንበኞችን በሚያስደስት መልኩ መሰራት እንዳለበትም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

የአቅም ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ ራስን የማዘመን እንዲሁም የቅንጅት ሥራዎች የማያቋርጡና ወደፊትም የሚቀጥሉ ተግባር መሆን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የሲቪል አቪዬሽን ደህንነት ዋና መምሪያ ያለፉት 14 ወራት የሪፎርም ሥራዎች በተጎበኘበት መርሐግብር በዘርፉ በቅንጅት የሚሠሩ የተለያዩ አካላት የጀመሯቸው ለአንድ ሀገራዊ ዓላማ በጋራ ተናቦና ተቀናጅቶ የመሥራት ባህል ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ተብሏል፡፡