ዓለምአቀፋዊ ዜና

ኅብረቱ አሥቸኳይ የተኩስ አቁም ጥሪ ለሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች አቀረበ

By Alemayehu Geremew

May 02, 2023

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ኅብረት አሥቸኳይ የተኩስ አቁም ጥሪ ለሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች አቀረበ፡፡

ኅብረቱ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ÷ ሱዳናውያን የውሃ፣ የጤና እና የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች መሰረታዊ ግብዓቶችን እንዲያገኙ ተፋላሚ ኃይሎች በአስቸኳይ ጦርነቱን አቁመው እንዲወያዩ አሳስቧል፡፡

ኅብረቱ ከተኩስ አቁም ጎን ለጎንም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለሱዳናውያን ሰብዓዊ አቅርቦት እና የተቀናጀ ድጋፍ እንዲያደርስም ጠይቋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ለጉዳዩ ዕልባት ለመሥጠት በፈረንጆቹ ባሳለፍነው ሚያዚያ 20 ላይ ከፍተኛ ዓለም አቀፋዊ ስብሰባ መጥራቱ ይታወሳል፡፡

በአፍሪካ ኅብረትና በተመድ የሚመራ ቡድን በሱዳን ፣ በቀጣናው ብሎም በአኅጉሪቱ የሚስተዋለውን ሁከትና አለመረጋጋት ለማስቆም ዓለም አቀፍ እርምጃዎችን እንደሚያስተባብርም ተጠቁሟል፡፡

የተሠጡት የውሳኔ ሐሳቦችም በአፍሪካ ኅብረት መርኅዎች የተደገፉ መሆናቸው ነው የተገለጸው፡፡

በአፈፃፀሙ ላይ ያተኮረ ስብሰባም በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ዛሬ ይካሄዳል።

#Ethiopia