የሀገር ውስጥ ዜና

በሐዋሳ 120 አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉበት ኤግዚቢሽን ተከፈተ

By ዮሐንስ ደርበው

May 02, 2023

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲዳማ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ያዘጋጀው 120 የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉበት ኤግዚብሽንና ባዛር በሐዋሳ ከተማ ተከፈተ፡፡

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ዋና አፌ ጉባዔ ፋንታዬ ከበደ ኤግዚቢሽንና ባዛሩን በከፈቱበት ወቅት እንዳሉት÷ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመቀነስ እየተደረገ ባለው ርብርብ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡

የኤግዚቢሽንና ባዛሩ መሪ ሐሳብ ”የኢንዱስትሪዎቻችን ምርታማነት ለብልፅግናችን” መሆኑ ተገልጿል፡፡

የቢሮው ኃላፊ አሻግሬ ጀምበሬ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት÷ በክልሉ 1ሺህ 81 ኢንዱስትሪዎች አሉ፡፡

የ “ኢትዮጵያ ታምርት” ፅንሰ ሐሳብን እውን ለማድረግም የሀገር ውስጥ አምራቾችን የማበረታት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች በጥራት ኢንዲያመርቱ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

የኢንዱስትሪ ምርትን በተለያዩ አካባቢዎች በማስፋት ለሸማች ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ለአራት ቀናት የሚቆየው ኤግዚቢሽንና ባዛሩ÷ ምርቶች በቀላሉ ወደ ሸማች እንዲደርሱ እና ሕብረተሰቡ ለሀገር ውስጥ ምርት ትኩረት እንዲሰጥ ያግዛል ነው የተባለው፡፡

በጥላሁን ይልማ

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!