አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርና ሚኒስቴር ከኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ጋር ከብሔራዊ ሉዓላዊነት ጎን ለጎን “በምግብ ሉዓላዊነት” ላይ እየሠራ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ከናይጄሪያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ ለተውጣጡ የሰራዊቱ ልዑካን ተሞክሮውን አካፍሏል።
በዚሁ ወቅት የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በሀገሪቱ ወቅታዊ የግብርና እና ቁልፍ ኢኮኖሚ ስኬት ላይ ገለጻ አድርገዋል።
የግብርና ሚኒስቴር ከመከላከያ ሚኒስቴር ጋር በመሬት ዝግጅት፣ አዝመራ እና ሌሎች የግብርና ሥራዎች ላይ እየሠራ መሆኑንም አብራርተዋል።
ሚኒስቴሮቹ ብሔራዊ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሠራዊት ካምፖች ዙሪያ የግብርና ሥራዎችን በማከናወን ላይ ስለመሆናቸውም አስረድተዋል፡፡
ስለ አምስቱ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምሶሶዎች (ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና የአይ ቲ እና ዲጂታል ኢኮኖሚ) ን በተመለከተም ሚኒስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በተጨማሪም በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በመስኖ ስንዴ እና ሌሎች ውጤታማ እየሆኑ ባሉ የግብርና ልማቶች ላይ ማብራሪያ መሰጠቱን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
የናይጀሪያ ልዑክም የግብርና ሚኒስቴር ከመከላከያ ሚኒስቴር ጋር በልማት ትብብር እያከናወነ ያለውን ሥራ አድንቋል፡፡
ልምዱንም በናይጀሪያ በስፋት እንደሚተገብረው ገልጿል፡፡