የሀገር ውስጥ ዜና

“ሰኔና ሰኞ” ድራማ ግንቦት 1 በፋና ቴሌቪዥን መታየት ይጀምራል

By Mikias Ayele

May 03, 2023

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 25 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) “ሰኔና ሰኞ” ድራማ ግንቦት 1 ቀን 2015ዓ.ም በፋና ቴሌቪዥን መታየት ይጀምራል፡፡

ድራማውን አስመልክቶ የፕሮዳክሽን አባላትና ተሳታፊ ተዋንያን እንዲሁም የፋና ቴሌቪዥን የማኔጅመንት አባላት በተገኙበት ዛሬ በመልካ ሆቴል መግለጫ ተሰጥቷል ።

በመግለጫው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠዉ  ÷ ፋና ቴሌቪዥን የተመልካቾቹን ፍላጎት ለማርካት ከትምህርታዊ ዝግጅቶችና ከመረጃ ባሻገር  በተለያዩ የመዝናኛ አማራጮች እየሰራ ይገኛል ብለዋል ።

ለባለሙያዎች መድረክ ለመፍጠር ፣ ጥበብን ለማበረታታትና የተመልካችን ፍላጎት በይበልጥ ለማሟላት አዲስ ተከታታይ ድራማ መቅረቡንም ነው የተናገሩት።

“ሰኔና ሰኞ” የሚል መጠሪያ በተሰጠው በዚህ  ተከታታይ ድራማ ላይ ከ100 በላይ ተዋንያን የተሳተፉበት ሲሆን÷ እንግዳሰዉ ሀብቴ (ቴዲ) ፣ ቃልኪዳን ታምሩ ፣ ሰለሞን ሙሄ ፣ሱራፌል ብስራት (አቡ ) እና ሌሎችም ዝነኛ ተዋንያን ይጠቀሳሉ።

ድራማው በ”ኢስተም ኢንተርቴይመንት” ተዘጋጅቶ የበረበ ሲሆን÷ በማህበረሰቡ የዕለት ተዕለት የህይወት ገጠመኞች ላይ ትኩረቱን አድርጎ በዋናነት ጭብጡን በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ አድርጎ በአስተማሪና በአዝናኝ  ትዕይንቶች ታጆቦ በ አራት ምዕራፎች እና በ60 ክፍል ለተመልካቾች የሚቀርብ ነው።

ድራማው በፋና ቴሌቪዥን ግንቦት1ቀን 2015ዓ.ም ማክሰኞ 3 ሰዓትከ10 ላይ መታየት  እንደሚጀምር በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

በቀጣይነትም ድራማው በተገለፀው ቀን እና ሰዓት ይተላለፋል።

በምንተስኖት ሙሉጌታ